ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል አረፉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 4/2011)የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባና የሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሳታፊ የነበሩት ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።

በሌላም በኩል በአሜሪካ ሂዩስተን ከተማ ከኢሳት አስተባባሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ አብይ ግርማ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ለእረፍት ወደ አሜሪካ ብቅ ባሉበት በድንገት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል በምርጫ 1997 ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሆነው መመረጣቸውንም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።

የሶማሊያ ወራሪ ሃይል በ1969 ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በካምቤራ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ላይ በናቪጌተርነት ሙያዊ አገልግሎት ለሃገራቸው በመስጠት ላይ እያሉ የነበሩበት አውሮፕላን ሶማሊያ ግዛት ማረፉን ተከትሎ ለ12 አመታት በሶማሊያ እስር ቤት ማሳለፋቸው ተመልከቷል።

በሁለቱ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት ከ12 አመታት በኋላ በ1981 ከወህኒ የወጡትና ከሌሎች ከባልደረቦቻቸው ጋር የክብር አቀባበል የተደረገላቸው ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል አየር ሃይሉ ሲበተን በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ የሃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸውን ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።

ነሐሴ 22 ቀን 1940 ዓም በሰሜን ሸዋ ደብረሲና ከተማ የተወለዱት ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል ከፍተኛ ትምህርታቸውን በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1963 በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የኤርክራፍት ራዳር ስልጠና በመውሰድ ሃገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩት ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል ትላንት እሁድ በድንገት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ለእረፍት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተጓዙት ሌተናል ኮለኔል ትርሲት ገብረመስቀል በአሜሪካ ኦሃዩ ግዛት በ71 አመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ትላንት እሁድ የካቲት 3 ቀን 2011 አመተ ምህረት ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢሳት የሒውስተን የድጋፍ ኮሚቴ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ አብይ ግርማ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

በሐገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሁም በኢሳት የድጋፍ ኮሚቴ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩት አቶ አብይ ግርማ የራሳቸውን የንግድ ተቋም አቋቁመው ሊቶ የተባለ የግል ማተሚያ ቤት ከፍተው ሲሰሩ ቆይተዋል።