ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍራንክፈርት የውውይት መድረክ ተዘጋጀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአውሮፓ የሚኖሩ ከ20ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን የሚያነጋግሩበት መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ መዘጋጀቱ ታወቀ።

ከነገ በስቲያ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያውያን ጋር በሚያደርጉት ውይይት ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ኢትዮጵያውያን ወደ ስፍራው መጓዛቸው ተመልክቷል።

ዛሬ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓሪስ ሲደርሱ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፍቅሩ ኪዳኔን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ተቀብለዋቸዋል።

በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ግብዣ ዛሬ ፈረንሳይ ፓሪስ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በነገው እለት ወደ ጀርመን ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በበርሊን በሚካሄደው የቡድን ሃያ ሃገራት በሚያዘጋጁትና በአፍሪካ ጉዳይ ላይ በሚመክረው ጉባኤ የሚሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ረቡዕ እለት ወደ ፍራንክፈርት በማቅናት ከኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

ከነገ በስቲያ ረቡዕ በፍራንክፈርት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ከ20ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የሚሔዱ ኢትዮጵያውያንም በዝግጅቱ እንደሚታደሙ መረዳት ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊዜ አንጻር ሌላ ተጨማሪ መድረክ እንደማይኖራቸውም በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ኩማ ደመቅሳ ለጀርመን ድምጽ ገልጸዋል።