ለጌዲዮ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታዎች ካልደረሱ አደጋው ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2011)ለጌዲዮ ተፈናቃዮች የሚያስፈልጉ አስቸኳይ ርዳታዎች ካልደረሱላቸው የሚደርሰው አደጋ የከፋ እንደሚሆን በአካባቢው የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።

ተፈናቃዮቹ አሁን ካሉበት አስከፊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሌሎች ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የመከሰት እድላቸው ሰፊ መሆኑንም ገልጸዋል ከህክምና ቡድኑ አባላት አንዱ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ።

የጤና ጥበቃን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣መላው ኢትዮጵያውያን፣መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶችና ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ አካላት ሁሉ አደጋ ላይ ላሉት ለነዚህ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የጌዲዮ ተወላጆች ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ እንዲፈናቀሉ ከተደረገ አንድ አመት ሊያስቆጥሩ ነው።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ተፈናቃዮቹን የት ወደቃችሁ ብሎ የሚጠይቅ አካል በመጥፋቱ ዛሬ ላይ የሕይወት መስዋዕትነትን እየከፈሉ ነው ያላሉ በስፍራው የተሰማሩት የህክምና ቡድን አባላት።

አሁን ላይም ለተፈናቃዮቹ የሚያስፈልጉ አስቸኳይ ርዳታዎች ካልደረሱላቸው የሚደርሰው አደጋ የከፋና ይሆናል ብለዋል ከህክምና ቡድኑ አባላት አንዱ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ።

የህክምና ባለሙያው እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ ካሉበት አስከፊ ሁኔታ አንጻር ህክምናውን ለመስጠት እንኳን አመቺ ሁኔታ አልተዘጋጀም።–አሁን ላይ ህክምናው እየተሰጠ ያለው ሰዎቹ ወድቀው በሚገኙበት ሜዳ ላይ መሆኑን በመጠቆም።

እንደ እሳቸው አባባል ከሆነ እነሱ ባሉበት የገደብ ወረዳ ብቻ 96ሺ የሚደርሱ ተፈናቃዮች አሉ።በዞኑ ደግሞ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ደግሞ እስከ ሁለት ሺ ይደርሳል።

96ሺ ከሚደርሱት ተፈናቃዮች ውስጥም 80ሺ ያህሉ ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ያለና አስቸኳይ የሚባል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

በተፈናቃዮቹ ላይ ያለው አደጋ እንዲህ በቀላል የሚገለጽ አይደለም።አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙ ለሌላ ተላላፊ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው ይላሉ።–የአተት፣የኩፍኝ፣የማጅራት ገትር፣የወባ፣የቆዳና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑንም ይናገራሉ።

ተፈናቃዮቹ በዚህ ብቻ ሳይሆን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችም ሊጠቁ እንደሚችሉም የህክምና ባለሙያው ሳይገልጹ አላለፉም።–አሁን ላይ ካለው ችግር አኳያ

እንደ ህክምና ባለሙያው አበባል ከችግሩ አስከፊነት የተነሳ በቀን ከሶስት እስከ አራት ሰዎች ይሞታሉ።መሞታቸው ብቻ አይደለም የመቅበሪያ ቦታም እየጠፋ ነው ያላሉ ።

አሁን በአካባቢው ለተፈጠረው ችግር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህክምና ባለሙያዎችን በዘመቻ ከማሰማራት ጀምሮ የጤና ጣቢያዎች በአካባቢው ገንብቶ አስቸኳይ ድጋፍ እስከማድረግ ያሉ ስራዎችን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት፣የሚመለከታቸው አካላት፣በአለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአጠቃላይ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ አካላት ሁሉ ወገንን በማዳኑ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።