ለውጡን ለማደናቀፍ በሚሰሩ አመራሮች ተቋማቸው እየተሽመደመደ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር1/2011)ለውጡን ለማደናቀፍ በሚሰሩ አመራሮች ተቋማቸው እየተሽመደመደ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች አመለከቱ።

በደል እየደረሰብን ነው ያሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች ለኢሳት በላኩት መግለጫ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመራው ለውጥ የተቋሙን ዋናና ምክትል ስራ አስኪያጆች እስከማባረር ቢያበቃም በድርጅቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ግብረአበሮቻቸው አሁንም ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፉት አስርት አመታት አዲስ ዘመን ጋዜጣን፥ ኢትዮጵያ ሄራልድን ቀጥሎም አልአለምንና በሪሳ ጋዜጦችን ሲያስተዳድር ቆይቷል።

ጋዜጦቹ በሶስቱም የአገዛዝ ዘመኖች የገዥዎች መሳሪያዎች ሆነው ማገልገላቸው ነው የሚነገረው፡፡

አሁንም ታዲያ ከዚህ አሰራሩ ለመላቀቅ ሲሞክር በተቋሙ ወስጥ ችግር መኖሩ ነው የተጠቆመው።

በ2010 ዓም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ  አዲስ መዋቅርና የሰራተኞች ድልድል ማስፈጸሚያና መመሪያ  ሰነድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞቹ ለኢሳት በላኩት መግለጫ አስታወቀዋል፡፡

ይህን ሰነድ ግን በወቅቱ የነበረው የድርጅቱ አመራር ቦርድ እንደማያውቀው ነው የገለጹት።

የቀድሞ አመራሮች በህገ ወጥ መንገድ ድልደሉን በማካሄድ የፓርቲ ሰዎችን ያለብቃታቸውና ደረጃቸው እስከ አራት ደረጃ አሳድገዋል።

ተቀናቃኝ  አመለካከት አላቸው የሚሉዋቸውን ሰራተኞች ደግሞ እስከ ሶስት ደረጃ ዝቅ አድርገው ተቋሙን ይበልጥ አዳክመዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ሳቢያም 24 ሰራተኞች ቅሬታ አቅርበው ጉዳዩን እስከ ፍርድ ቤት ማድረሳቸውን ሰራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ቅሬታ ያደረባቸው ሰራተኞች ደግሞ ብንከስ ምን እናመጣለን በሚል በፍትህ ተቋማት ላይ ባለመተማማናቸው ችግሩን በሆዳቸው ይዘው ማስታመምን መረጠዋል ነው ያሉት፡፡

ወደ ፍርድ ቤት የሄዱት ግን ጉዳያቸው ከመጀመሪያው ፍርድ ቤት አልፎ ወደ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ቀርቦ  የድልድል ሰነዱ እንዲቀርብ እስከመታዘዝ ደርሷል፡፡

ነገር ግን በቀድሞዎቹ ዋና እና ምክትል ስራ አስኪያጆች የሚመራው ቡድን የነበረውን የድልድል መመሪያ ማቅረብ ትቶ ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ይሕንኑ አቅርቦ ጉዳዩን ለጊዜው ለማዳፈን ሞክሮ ነበር ብለዋል፡፡

ችግሩ ከታወቀ በኋላ መዝገብ ቤት ያለው ፋይል ይጣራ ሲባል የተፈጸመው ወንጀል መሆኑ እየታወቀና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተመርቶ እንዲመረመር መደረግ ሲገባው አመራሩ ለርሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን የኮሚቴ አባል በማድረግ ጉዳዩ እንዲዳፈንና የተከሰሱት የመዝገብ ቤት ሰራተኞችም በነጻ እንዲሰናበቱ አድርጓል ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ የመጣውና በወጣት የተተካው አመራር በመስሪያ ቤቱ ያለውን የተከማቸ በደልና ኢፍትሃዊ አሰራር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም ለውጥ አለመኖሩን ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞቹ አመልክተዋል፡፡

ሰራተኞቹ እንደሚሉት አሁን አመራሩን የከበቡት በህገ ወጥ መንገድ የተቀጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡

ይህ የሙስና ሹመት የብዙ ዜጎችን የመወዳደር እድልና የውስጥ እድገት አምክኗል ባይ ናቸው ሰራተኞቹ፡፡

መንግስት ሙስናን የማይሸከም ትውልድ እፈጥራለሁ እያለ በአንድ ተቋም ሌቦች በአመራር ቦታ እንዲቀጥሉ መተባበር የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑ ሊታወቅ ይገባልም ብለዋል፡፡