ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት የተሰጠው ብድር 4 ቢሊየን ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 29/2010) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት የሰጠው ብድር 4 ቢሊየን ብር መድረሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

የመንግስት ኩባንያዎችም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በድር ለማግኘት በተቸገሩበት በአሁኑ ወቅት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወሰዱት ገንዘብ አኪር የተባለውን የኮንስትራክሽን ድርጅት መግዛታቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተበዳሪዎች ገንዘብ ለማቅረብ በከፍተኛ ደረጃ በተቸገረበት በአሁኑ ወቅት ለአቶ ተክለብርሃን አምባዬ የሚሰጠው ብድር መቀጠሉና 4 ቢሊየን ብር መድረሱ አነጋጋሪ ሆኗል።

የመንግስት ኩባንያዎችም ሆነ የግል ነጋዴዎች ብድር ለማግኘት አመት ያህል ወረፋ በሚጠብቁበት ብድሩ ሲለቀቅም ከ50 በመቶ በላይ በሚያገኙበት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ በባንኩ ገንዘብ ሌላ ኩባንያ እስከመግዛት መድረሳቸውን የባንኩ ምንጮች ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰራር ፈጽሞ በማይቻልበት ሁኔታ ከመምሪያ ውጪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደ 1 ቢሊየን ብር የኢንጂነር አወጣህኝ ኪሮስ ንብረት የሆነውን አኪር ኮንስትራክሽንን መግዛታቸውን የባንኩ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደው 1 ቢሊየን ብር ለኩባንያው ግዢ የዋለው ከባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ እውቅና ውጭ እንዳልሆነም ተመልክቷል።

ከባንኩ የቦርድ ሰብሳቢነት በኋላም ከቦርድ አባልነት የተነሱት የሙስናው ንጉስ በሚል የሚታወቁት አቶ አባይ ጸሃዬ አሁንም በባንኩ ውስጥ ተጽእኗቸው ያልተገደበ እንደሆነም የባንኩ ምንጮች ይገልጻሉ።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የትግራዮች የበላይነትን ለማስጠበቅ ከሚጠቀሙባቸውና ልዩ ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው ባለሃብቶች አንዱ ናቸው።

አቶ ተክለብርሃን አምባዬ የባንኩ ፕሬዝዳንት ከሆኑት ከብአዴኑ አቶ በቃሉ ዘለቀ ጋር የፈጠሩትም ቅርበትና የጥቅም ግንኙነት ሒደቶችን ይበልጥ እያቀለሏቸው እንደመጡም ተመልክቷል።

አቶ ተክለብርሃን አምባዬ ለባንኩ ፕሬዝዳንት ለአቶ በቃሉ ዘለቀ እንዲሁም የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ለነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ቪላ ቤት ገንብተው ማስረከባቸውንም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮች መረዳት ተችሏል።

በቅርቡ የተመረቀውንና ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚገኘውን ዛግዌ የተባለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ በተመሳሳይ የወሰዱትና የሰሩት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ መሆናቸው ታውቋል።

የኤሌክትሪክና የካሜራ መስመሮችን የመዘርጋትና የመግጠሙን ስራ የአቶ ተክለብርሃን አምባዬ  ወንድም ሲወስዱት የቢሮ እቃዎቹን የማቅረቡ ስራ ደግሞ ለአቶ ተክለብርሃን አምባዬ ባለቤት መሰጠቱም ታውቋል።

አቶ ተክለብርሃን አምባዬ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ባላቸው ተጽእኖ ከፍተኛ ብድር ከመውሰድ ባሻገር ልዩ ልዩ የባንኩን የኮንስትራክሽን ስራዎች ያለጨረታ እየወሰዱ ሲከውኑ መቆየታቸው ተመልክቷል።

በዚህ ረገድ መገናኛ አካባቢ የተገነባውና ሕዳሴ የተባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ ከጨረታ ውጪ በአቶ ተክለብርሃን አምባዬ የኮንስትራክሽን ድርጅት የተገነባ ነው።

የግንባታውን ወጪ በተመለከተ ባንኩ እስካሁን ይፋዊ ሪፖርት አለማውጣቱም አነጋጋሪ ሆኗል።

የቢሮ እቃዎቹን ከጣሊያን በሚመጡ ቁሶች ለመሙላት ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም ብዙዎቹ የቢሮ እቃዎች የቻይና ስሪቶች ሆነው መገኘታቸውንም የባንኩ ምንጮች በዝርዝር ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቅርቡ የኢትዮጵያን ሆቴል የገዙት አቶ በላይነህ ክንዴም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱት ብድር 2 ቢሊየን ብር መድረሱን ምንጮቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

ከባንኩ ጋር ስላላቸው የተለየ ግንኙነት የተመለከተ ነገ የለም።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ደረጃ የሰጠውን ብድር መሰብሰብ እንደተቸገረም ታውቋል።

ብዙዎቹ እዳውንም ሆነ ወለዱን መክፈል አለመቻላቸውም ተመልክቷል።

ባንኩ ጤናማ ሁኔታ ላይ ነው በሚል የባንኩ ፕሬዝዳንት የተበላሸ ብድር በማለት እዳውን ለመሰረዝ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ሆኖም ይህንን የማድረግ ስልጣን እንደሌላቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ ያስገነባው ህንጻ ውስጥ ቢሮ መከራየቱም ታውቋል።

የጥቅም ግጭት ያስከትላል በሚል ተቃውሞ ከወዲሁ ተቀስቅሷል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ በቅርቡ አዲስ አበባ ለገሃር አካባቢ ያስገነባውን ህንጻ ሁለት ፎቅ ሙሉ ብሔራዊ ባንክ የተከራየበት ምክንያት ቢሮ ጠበበኝ በሚል ሲሆን በከተማዋ ካሉት ህንጻዎች የሕወሃት ንብረትን መርጦ የተከራየበት ምክንያት አልተገለጸም።

ወጋገን ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደና ባልተመለሰ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ከተገነቡ የሕወሃት ኩባንያዎች አንዱ ነው።

ጥቂት ሌሎች ባለአክሲዮኖችም ባለድርሻ ሆነው እንደሚሳተፉ ታውቋል።