ለተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የሚመረጡ ሃገራት የሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ግምት ውስጥ መግባት እንደሚገባው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2009)

ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የሚመረጡ ሃገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ታሪካቸው ግምት ውስጥ መግባት እንደሚገባው አለም አቀፍ ምሁራን አሳሰቡ።

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ የፌታችን ጥቅምት ወር ሁለት አዳዲስ አባል ሃገራትን ለምክር ቤት ለመምረጥ ልዩ ስብሰባን እንደሚያካሄድ ዲቬክስ የተሰኘና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራ መጽሄት ዘግቧል። ይሁንና ጉባዔው የአባል ሃገራትን ምርጫ ሲያካሄድ የእጩ አገራት የሰብዓዊ መብት ሁኔታና ታሪክ መመልከት እንዳለበት ምሁራን ጥሪ ማቅረብ መጀመራቸውን መጽሄቱ አመልክቷል።

በአውስትራሊያ ናሽናል ዩኒቨርስቲ የህግ ማሻሻያና የማህበራዊ ፍትህ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሲሞን ራይስ ለምክር ቤቱ አባልነት የሚመረጡ ሃገራት ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ታሪካቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ስፍራ እየተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፊታችን ጥቅምት ወር ሁለት አዳዲስ አባላትን ለመሰየም በሚካሄደው ምርጫም የሃገራትን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ዋነኛ መስፈርት ማድረግ እንዳለበት ምሁሩ አሳሰበዋል።

በአውስትራሊያ የሂውማን ራይስት ዎች ተወካይ የሆኑት ኢሌየን ፐርሰን በበኩላቸው በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው የሰላ ትችት የሚቀርብባቸው ኢትዮጵያ፣ ቻይና ሳውዲ አረቢያ በድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት መመረጣቸው የሚያስተች ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው አመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ጉባዔ ባካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ አባል እንድትሆን መምረጡ የሚታወስ ሲሆን፣ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በምርጫው ላይ ተቃውሞን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ይኸው ተቃውሞ በአዲስ መልክ መቅረብ የጀመረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለምክር ቤቱ የሚመርጣቸውን አባል ሃገራት በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው መመዘን እንደሚገባቸው እነዚሁ አካላት ጥሪ ማቅረባቸውን ዴቬክስ መጽሄት በዘገባው አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ለሁለት አመት በአባልነት ከተመረጡ ሃገራት መካከል አንዷ ብትሆንም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያና እስራት ለመመርመር ላቀረበው ጥያቄ ፈቃደኛ ሳትሆን መቅረቷ ይታወሳል።

ሃገሪቱ በሰብዓዊ ምክር ቤቱ አባል ሃገር ሆና እያለች ለድርጅቱ መርሆዎች ተገዢ አለመሆኗን ሂውማን ራይስት ዎችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ባለሙያዎችና ድርጅቶች ለአባል ሃገራት ድምፅን የሚሰጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ልዩ ትኩረትን መስጠት እንዳለባቸው ጥሪ ማቅረባቸውን መጽሄቱ በዘገባው አመልክቷል።