ህወሃት ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠርበትን እቅድ ለመንደፍ መቀሌ ከትሟል

ህወሃት ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠርበትን እቅድ ለመንደፍ መቀሌ ከትሟል
(ኢሳት ዜና ግንቦት 02 ቀን 2010 ዓ/ም) የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ተከታታይ የሆኑ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበዙበት ህወሃት፣ ሙሉ ስልጣኑን መልሶ የሚቆጣጠርበትን ስልት ለመንደፍ መቀሌ ላይ ከትሞ ጥናት እያደረገ ነው ።
ህዋሃት እራሱን ከአንዳንድ የፌደራል መንግስት የስልጣን ቦታዎች በማራቅና ህወሃት የሌለበት በማስመሰል እንዲሁም የፌደራል መንግስትን የማስፈጸም አቅም በተለያዩ እንቅፋቶች በመክበብ እና በማደነቃቀፍ ህወሃት የሌለበት ነገር ውጤታማ አይሆንም ወደ ሚያስብል አስተሳሰብ ህዝቡንና የድርጅቱን አባላት ለመክተት እቅድ በመንደፍላይ ነው። በተለይ ሙሉ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ በሚገኘው የደህንትና የመከላከያ ተቋማት አማካኝነት የተለያዩ ግጭቶችን በመቀስቀስና አለመረጋጋት በመፍጠር ተቀባይነቱን ለማጉላት በስልትነት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል ።
ህወሃት ባደለባቸውና በሚተማመንባቸው ባለሃብቶች እንዲሁም በፓርቲው የንግድ ተቋማት አማካኝነት አገራዊ ኢኮኖሚውን ችግር ውስጥ በመክተትና መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጡን ቀርፋፋ በማድረግ ህዝቡ “የድሮው ይሻለናል” ብሎ ተመራጭ ለመሆን ማቀዱንም ምንጮች ገልጸዋል።
እንዲሁም ታዳጊ ክልሎችን ወይም ኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚላቸውን በድምጽ ወደ ሚሳተፉበት አሰራር በማምጣት ዋናዎቹን የኦህዴድና የብአዴን ለውጥ ፈላጊዎች አስተሳሰብበ አናሳ ወይም በጠባብ አመለካከት አራማጆች አስተሳሰብ የመተብተብና እርምጃዎችን የማንገራገጭ የሴራ ፖለቲካን ለመከተል እቅዶችን እየነደፈ ነው ።
ህወሃት ኦህአዴድ እና ብአዴን የራሳቸውን የውስጥ ድክመት በህወሃት በማሳበብ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንዲጠላ እንዳደረጉት ያምናል። ከእነዚህ ሃይሎች ጋር የሚኖረውን የወደፊት ግንኙነት ለመወሰን የተለያዩ አማራጮችን በማጥናት ላይመሆኑንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።