ሁሉም ወገኖች ለሰላም እንዲሰሩ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 4/2011) በአዲስ አበባ የተፈጠረው ግጭት እንዲቆምና ሁሉም ወገኖች ለሰላም እንዲሰሩ ተጠየቀ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መግለጫ በመስጠት ወጣቶች ከእርስ በእርስ ግጭት ራሳቸውን እንዲያርቁ ጥሪ አድርገዋል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና ሰማያዊ ፓርቲ በተፈጠረው ግጭት ላይ ያተኮረ መግለጫ ዛሬ መስጠታቸው ታውቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ በሰንደቅ ዓላማ መነሻነት የተፈጸመው ግጭት ድርጅቱን እንደማይወክል አስታውቋል። የፌደራል ፖሊስ ጸጥታን ለማስከበር አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ለሶስተኛ ቀን የቀጠለው የአዲስ አበባው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሰንደቅዓላማና አርማ መነሻ ሆኖ በተጀመረው በዚሁ ግጭት እስከአሁን የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ እየተገለጸ ሲሆን ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልም ተመልክቷል።

በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በአየር ጤናና በአንዳንድ የአዲስ አበባ መውጪያ አካባቢዎች ዛሬም

ግጭቶች መከሰታቸው የተገለጸ ሲሆን የሰው ህይወት ላይ አደጋ መድረሱም ታውቋል።

በርካታ ተሽከርካሪዎች የመስታወት መሰባበር ጥቃት እንደተፈጸመባቸውም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በኦሮሞ ወጣቶችና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት እንዲቆም ከየአቅጣጫው መልዕክቶችና ጥሪዎች በመተላለፍ ላይ ናቸው።

በትላንትናው ዕለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ መሪዎች ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል መንግስት ህገወጥ ተግባራትን ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ አስታውቀዋል።

ፖሊስ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነቱን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ወጣቶች በአስቸኳይ ከግጭት እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ከኮሚሽነሩ ጋር መግለጫ የሰጡት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀምንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ልዩነቶችንን ተቀብለን ወደፊት ካልተራመድን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አንችልም በማለት ወጣቶች በእንደዚህ ዓይነት አጀንዳዎች ጸብ ውስጥ እንዳይገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ በአዲስ አበባ እየተፈጸመ ያለው ተግባር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

አሁን እየታየ ያለው ግጭት እና ያልተገባ ፉክክር ኦነግን የማይወክል ነው ሲሉ አቶ ኢብሳ ነገዎ በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።

ሌሎች ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ወጣቶች በአነስተኛ አጀንዳዎች ላይ ግጭት ውስጥ ገብተው የተጀመረውን የሰላም ሂደት እንዳያደናቅፉ ጥሪ አድርገዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ አመራር አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ ወጣቶች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አድርገዋል።

ሰማያዊ ፓርቲም በአመራር አባሉ አቶ አበበ አካሉ በኩል በሰጠው መግለጫ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ ዓይነት ያልተገባ ተግባር ራሱን እንዲያርቅ ጠይቋል።

ሁለቱም ፓርቲዎች መንግስት ችግሩ ከመባባሱ በፊት እርምጃ እንዲወስድም ጥሪ አድርገዋል።

በተያያዘ ዜና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ መጋጨት በሌለብን ጉዳይ እንድንጋጭ የሚፈልጉ አካላት በመኖራቸው ህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ የተፈጠረውን ግጭት ኦነግን እንደማይወክል እየተገለጸ ሲሆን ከጀርባ የህወሃት ቡድን ግጭቱን እያቀጣጠለው እንዳለ እየተነገረ ነው።

በሌላ በኩል የትግራይ ክልል መንግስት ወደ ሀገር ቤት ለሚገባው የኦነግ ሰራዊት በዛላምበሳና በአዲግራት የቁርስና የምሳ ግብዣ እንደሚያደርግም አስታውቋል።