ሁለቱ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ድባብ አሳስቦናል አሉ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 10/2010) ሁለቱ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ድባብ እንዳሳሰባቸውና አለመቻቻልና ከፋፋይ ፖለቲካ እየተባባሰ መምጣቱ ለሀገሪቱ አደጋ ነው አሉ።

ባራክ ኦባማና ጆርጅ ቡሽ የወቅቱን ፕሬዝዳንት ስም ሳይጠቅሱ አሁን ያለው አስተዳደር እየፈጠረ ያለው የከፋፋይና የማስፈራራት ፖለቲካ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።

ባራክ ኦባማና ጆርጅ ቡሽ በተለያየ ወቅት በተለያየ መድረክ ላይ ስለወቅቱ የሀገራቸው ጉዳይ ንግግር አድርገዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ንግግር ባደረጉበት ወቅትም የፕሬዝዳንት ትራምፕን ስም ባይጠቅሱም አስተዳደሩ እየፈጠረ ያለው የከፋፋይና የማስፈራራት ፖለቲካ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የዶናልድ ትራምፕን ስም ሳይጠቅሱ ሀገሪቱ እየተመራች ያለችበትን አካሄድ ነቅፈዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች በዘልማድ ተከታዮቻቸውን ከመንቀፍ የሚቆጠቡ ቢሆንም ባራክ ኦባማ የረጅም ጊዜ ዝምታቸውን በመስበር ንግግር አድርገዋል።

ኦባማ በተለይ የትራምፕ አስተዳደር ኦባማ ኬር በመባል የሚታወቀውን ብሎም በእሳቸው የአስተዳደር ዘመን የጸደቀውንና አሜሪካኖች ክፍያው ተመጣጣኝ የሆነ የጤና ኢንሹራንስ እንዲያገኙ የሚያደርገውን ሕግ ለመሻር መንቀሳቀሳቸውን ነቅፈዋል።

እንዲሁም ከሙስሊም ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚመጡ ተጓዞች ላይ የጣሉት ማዕቀብን አስመልክተው ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

አሜሪካኖች የመከፋፈልና የፍራቻ ፖለቲካን እንደማንቀበልና እንደምንቃወምም ለአለም በግልጽ ማሳወቅ ይገባናል ሲሉ ኒውጀርሲ ውስጥ በምትገኘው ኒው ዋርክ ከተማ ውስጥ በተካሄደ የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አክለውም ለዘመናት የቆየና ያረጀ ከፋፋይ ፖለቲካ አሁን መልሶ ሲመጣ ልንቀበለው አይገባም ብለዋል።

ከ50 አመት በፊት መፍትሄ የተሰጠው የከፋፋይ ፖለቲካ አካሄድን መልሶ ለማምጣት እየተሞከረ ነው።- አሁን ግን 21ኛው ክፍለ ዘመን እንጂ 19ኛው ክፍለ ዘመን አይደለም ብለዋል።

ከባራክ ኦባማ ቀደም ብለው በኒዮርክ በሌላ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ጆርጅ ቡሽ ግትርነትና የሌላውን የተለየ የፖለቲካ እምነትና አመለካከት ያለመቀበል ባህል እየተስፋፋ መምጣቱንና ፖለቲካችን ለፈጠራ ወሬዎች፣ለሴራና አሻጥር እየተጋለጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መቻቻል፣ልዩነትን መቀበልና መግባባት ለዘመናት በአሜሪካውያን ዘንድ ትልቅ ዋጋ የምንሰጠው ሕሴታችን ነው ሲሉ መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።