710 ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ባለድርሻዎቹ ሆነው መገኘታቸው ታወቀ

ኢሳት (የካቲት 6 ፥ 2009)

የብሄራዊ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻ እንዲመልሱ ባስተላለፈው መመሪያ እስከአሁን ድረስ 710 የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለድርሻዎቹ መገኘታቸው ተገለጸ።

ባንኩ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኙ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለብሄራዊ ባንክ የተጠየቁትን ዝርዝር በመስጠት ላይ ሲሆን፣ በእስከአሁኑ እርምጃ 700 የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለድርሻዎቹ ተለይተው መታወቃቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ለባንኩ የቀረበን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁንም ድረስ የመለየት ስራ በማከናወን ላይ በመሆናቸው ቁጥሩ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

የብሄራዊ ባንክ የውጭ ሃገራዊ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ መያዝ የለባቸውም በማለት ከወራት በፊት አክሲዮን ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻቸውን እንዲመልሱ ማሳሰቡ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 34 የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በድምሩ ከ140ሺ በላይ አክሲዮኖቻቸው የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተይዘው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

እስካሁን ሪፖርት በተደረገው መረጃ መስረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ድርሻ ከ350 እስከ 400 ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለውም ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።

በአሁኑ ወቅት የአዋሽ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ባንኮች ከትውልደ ኢትዮጵያውያን የተመለሱ አክሲዮኖችን ለመሸጥ ጨረታ አውጥተው የሚገኝ ሲሆን፣ ለጨረታ የሚቀርቡት አክሲዮኖች የሚያስገኙት ትርፍ በቀጥታ ለመንግስት ገቢ እንደሚደረግ በብሄራዊ ባንክ መመሪያ ተደንግጓል።

የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የአክሲዮን ድርሻቸውን በገዙበት ዋጋ እንዲመልሱ በዚሁ መመሪያ ትዕዛዝ መቀመጡ ተመልክቷል።

ይሁንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከአመታት በፊት አክሲዮን ለመግዛት ያወጡት ገንዘብ አሁን ካለው የብር የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ዕርምጃው በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በባንኮች በጨረታ በመቅረብ ላይ ያሉ እነዚሁ የአክሲዮን ድርሻዎች ከፍተኛ ዋጋ እደሚያወጡም ባለሙያዎቹ አክለው አስረድተዋል።