2 ሺህ 700 የ አዳማ (የናዝሬት) ከተማ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ

ግንቦት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-2 ሺህ 700 የ አዳማ(የናዝሬት)ከተማ ነዋሪዎች  “ለሀዲድ ግንባታ “በሚል ያለ ምትክ ቦታ ከይዞታቸው በግዳጅ ተፈናቀሉ።

ተፈናቃዮቹ፦”ንብረታችንና ቤታችን በማናውቃቸው ሰዎች ተዘርፏል”  ይላሉ።
ሪፖርተር እንደዘገበው፤ለምድር ባቡር ሐዲድ ሥራ  ተብለው ከያዙት ሕጋዊ ቦታ ያለ ምትክ ቦታ በግዳጅ እንዲፈናቀሉ ከተወሰነባቸው    ከ2700 የአዳማ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪዎች  መካከል ፤ግምት የተሰጠው ለ 719ኙ ብቻ ነው፡፡

ለ2,700 ሦቹ ተፈናቃዮች ምትክ ቦታ ባልተመቻቸበት፣ እንዲሁም  ግምት ተሠርቶ ያልተከፈላቸው እና የግምት ሥሪቱ ስህተት አለው በማለት ቅሬታ ያቀረቡ 580 ሰዎች ቅሬታቸው በመታየት ባለበት ወቅት፣ ህጋዊ የመኖርያ ቤታቸው በኃይል እንዲፈርስ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን  ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

እነኚሁ  በሺዎች ሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እንደሚሉት፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ ሚያዝያ 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ፦” በአስቸኳይ በሦስት ቀን ውስጥ ንብረታችሁን እንድታነሱ”  የሚል ማስታወቂያ መለጠፋቸውን ተከትሎ፣ ወደ ከንቲባው ቢሮ በመሄድ አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ከንቲባው “ ሊያናግራቸው ፈቃደኛ አልሆኑም።

ይልቁንም ፦” ለምን ቢሮዬ መጣችሁ?” በማለት ነው የመለሷቸው።
ከዚያም ከንቲባው  ከሁለት ቀን በሁዋላ ማለትም ሚያዚያ 10 ቀን በቦታቸው  ላይ በመገኘት፦” በተሰጣችሁ ቀን ውስጥ ካላነሳችሁ በግሬደር እንደዋለሁ!” በማለት  ማስጠንቀቂያ አዘል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ “ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማናውቃቸው ግለሰቦች ንብረታችንና ቤታችን ፈርሶና ተዘርፎ ምደረ በዳ ሆኗል፤” ብለዋል፡፡
የንብረት ገማቾች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ለማ አስፋው ፣ ለተፈናቃዮች የሚሰጠው ግምት መጀመርያ ወደ አዳማ  ከዚያም ወደ ምድር ባቡርና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተልኮ ከታየ በኋላ ወደ አዳማ ቅርንጫፍ በሚላክበት ጊዜ በተፈጠረው መዘግየት ግምት ሳይከፈል መቆየቱን ጠቅሰው፣ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ግምት የተከፈላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የስም ስህተት ያለባቸውና አቤቱታ አቅርበው ጉዳያቸው እየታየ ካሉ ተፈናቃዮች በስተቀር አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ግምት እየተከፈላቸው ነው ያሉት አቶ ለማ፤ “ተፈናቃዮቹ  ቤታቸው የፈረሰው፤ በውይይት እንጂ በኃይል አይደለም”በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል።
እርሳቸው ይህንን ቢሉም የአዳማ ከንቲባ  ሚያዝያ 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ባስተላለፉት ትዕዛዝ፣ ለተፈናቃዮቹ የባቡር መንገድ በሚገነባበት ቦታ ላይ ላለው የመኖርያ ቤታቸው ካሳ እንደሚከፈል ገልጸው፣ “ይሁን እንጂ እናንተ ያላችሁበት ቦታ በአስቸኳይ ስለሚፈለግ በቦታው ላይ ያለውን ንብረት  በሦስት ቀን ውስጥ  እንድታነሱ! ይህ ሳይሆን ቢቀር መንግሥት ይህን ንብረት ወስዶ ቤቶቹን  የሚያነሳ መሆኑን እንገልጻለን፤” በማለት ግምት ያልተከፈላቸው ሰዎች ሳይቀር ቤታቸው እንደሚፈርስ አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ፦”ለሚፈርሰው ቤት የተሰጠን ግምት የተሳሳተ ነው” በማለት ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎች፣ “ቅሬታችንን ተቀብሎ እየተመለከተው ያለው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሊያጣራ ሲመጣ፤ ቤታችን ከፈረሰ ምን ዓይነት መረጃ ሊያገኝ ይቻላል?” የሚል ጥያቄ ለከንቲባው ሲያቀርቡ፣ “መረጃው በኮምፒዩተር ተይዟል” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ነዋሪዎቹ አውስተዋል፡፡

“ ቤታችን የፈረሰብንስ ሰዎች የት እንግባ?”በማለት   ላነሱላቸው ጥያቄ፣ከንቲባው፦ “ለፈረሰባችሁ ቤትና ለቤት ኪራይ የምትከፍሉት ገንዘብ አንድ ላይ ታስቦ ነው የተሰጣችሁ፤” ብለው እንደመለሱላቸውም  ተናግረዋል፡፡
ጋዜጣው የጠቀሳቸው አንድ ተፈናቃይ ፣ “ቤታችሁን በሦስት ቀን ውስጥ አፍርሱ” የሚለውን የከተማውን ከንቲባ ትዕዛዝ ተከትሎ የከተማው ታጣቂዎች በየቦታው እየተዘዋወሩ የተወሰኑ ሰዎችን በማስፈራራት ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ማስገደዳቸውን ጠቅሰው፤ “ካሳ ሳይከፈለንና ምትክ ቦታ ሳይሰጠን ቤታችንን አናፈርስም፤” በማለት የተቃወሙ በርካታ ተፈናቃዮች  ደግሞ ቤታቸውን የገነቡበት ቆርቆሮና ብረት በሌሊት በሌቦች መዘረፉን ተናግረዋል።
ተጎጂዎቹ ያነሷቸውን አቤቱታዎች  በማስመልከት ከንቲባው ምላሽ እንዲሰጡ የተደረገው ሙከራ፣ “ስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ሳይሳካ መቅረቱም ተመልክቷል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣በአፋር እና በጋምቤላ ክልሎች ነዋሪዎችን በልማት ስም ከህጋዊ ይዞታቸው ያለ አንዳች ካሳእና ምትክ ቦታ የማፈናቀል ተግባሩ  በስፋት ቀጥሏል።

መንግስት በተለይ “ትራንስፎርሜሽን”የሚል እቅድ ነድፌያለሁ ካለ በሁዋላ   በስፋት የተያያዘውን ዜጎችን የማፈናቀል ተግባር የተከታተሉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ፦”አንድን አገር ለማልማት የዚያ አገር መንግስት እና ህዝብ በመተጋገዝ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚኖርባቸው የሚስተባበል ሀቅ አይደለም ።ይሁንና ለልማት መስዋዕት መከፈል አለበት ማለት፤ ድሆችን ሜዳ ላይ እየጣሉ በመግደል በመቃብራቸው ላይ ባዶ ህንፃ መገንባት አይደለም” ብለዋል።

የአቶ መለስ መንግስት ከዜጎች ህይወት ይልቅ ለቁስ ከፍ ያለ ግምት እንዳለው የታዘበው የፍትህ አምደኛ ጋዜጠኛ  ዓለማየሁ ገላጋይ ፦”የአንድ ኢትዮጵያዊ ዋጋው ምን ያህል ነው?” በማለት መጠየቁ አይዘነጋም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide