ፖሊሶች በድብደባ አንድ ሰው ገደሉ

ሰኔ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እንደ ሪፖርተር ዘገባ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ የነበረው አቶ ሀሚድ ወዳጆ  ህይወቱ ያለፈው ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት ላይ ቄራ አካባቢ በፖሊሶች በደረሰበት ከባድ ደብደባ ነው።

አቶ ሀሚድ በፖሊሶች ተደብድቦ ሕይወቱ ሊያልፍ የቻለው ከጓዳኞቹ ጋር ሲዝናኑ  አምሽተው በዕለቱ የ2012 የአውሮፓ ዋንጫ ተፋላሚ የነበሩትን የጀርመንን እና የፖርቹጋልን ጨዋታን በሚመለከት የተወሰኑት ‹‹ወደ ቤት እንግባ›› ሲሉ የተወሰኑት ደግሞ ‹‹ጨዋታውን እንመልከት›› በማለት ሲነጋገሩ  የሰሙ ፖሊሶች፦‹‹ለምን ትረብሻላችሁ?›› በማለት  ያነሱትን ጥያቄ  ተከትሎ  በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

በወቅቱ አብሮት የነበረው ጓደኛው በበኩሉ  እንደተናገረው፣ ቄራ አካባቢ ሲዝናኑ ቆይተው መስቀልኛ ጫፍ ላይ ሲደርሱ ‹‹ኳስ እንይ ወይስ ወደቤት እንግባ?›› እየተባባሉ ሲነጋገሩ፣ አራት ዱላ የያዙና ሁለት ክላንሽኮቭ መሣሪያ የያዙ ስድስት ፖሊሶች ተጠግተዋቸው ‹‹ምን ያስጮሀችኋል? ለምን ትረብሻላችሁ?›› ብለው ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል፡፡
እነሱም፤መኖሪያቸው ጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም በመሆኑ ላዳ ኮንትራት ይዘው ወደ ቤታቸው ለመግባት እየተነጋገሩ እንጂ እየረበሹ አለመሆኑን ለፖሊሶቹ መናገራቸውን የገለጸው ይኸው የሟች ጓደኛ፣ ፖሊሶቹ ዝም እንዲሉ በመሳደብ ሲያስጠነቅቋቸው፣ ሟች ‹‹ምን አደረግን?›› ብሎ  በመጠየቁ  ክርክር መጀመሩን ገልጿል፡፡
በምልልሱ እየተናደዱ የመጡት ፖሊሶች ሟችንና አንደኛውን ጓደኛቸውን በዱላ መምታት ሲጀምሩ ሟች፣ ‹‹ፖሊስ ሆናችሁ ከመታችሁን ምን ዋስትና አለን? ለምን ትደበድቡናላችሁ?›› እያለ  መጮኹን የገለፀው  የሟች ጓደኛ፤ከዚያም  ሦስቱ ፖሊሶች እሱን ለብቻው ነጥለው ከጓደኞቹ ራቅ በማድረግ ክፉኛ እንደደበደቡት  ተናግሯል።

በዚህን ጊዜ ቀሪዎቹ   ሦስቱ ፖሊሶች እነሱን በመሣርያ እያስፈራሩ እንዳይገላግሉት ማድረጋቸውን የጠቆመው ይኸው የሟች ጓደኛ፤በዚህም ምክንያት  አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎፋ ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን  ተናግሯል፡፡
ይሁንና እዚያም ቢሄዱ  የጎፋ ፖሊስ ጣቢያ ድርጊቱን ከማዳመጥ የዘለለ ዕርዳታ ሊያደርግላቸው  አልቻለም።

በፖሊስ ጣቢያው ምላሽ ተስፋ ቆርጠው  በፖሊሶች እየተደበደበ ወደነበረው ጓደኛቸው ሲመለሱ ፖሊሶቹ   ሟችን ለቀውት  ያገኙታል።

ከዚያም  ከፖሊሶች ድብደባ የተረፈውን  ጓደኛቸውን ይዘው  ወደ ቤታቸው በመጓዝ ላይ እያሉ፤  ሟች እግሩ እየተሳሰረ መሄድ ያቅተዋል።

የስልክ እንጨት ተደግፎ ለመቆም ሲሞክር፤ በድብደባ የተጎዳው እጁ ሊይዝለት   ስላልቻለ ራሱን ስቶ ይወድቃል፡፡
በዚህን ጊዜ በአካባቢው ያገኟቸውን ሁለት ግለሰቦች ዕርዳታ ጠይቀው ከወደቀበት ቦታ በማንሳትና  ወደ አስፋልት በማውጣት በላዳ ታክሲ  አሳፍረው ቄራ አካባቢ ወደሚገኘው ቅድስት ማርያም ክሊኒክ ሲያደርሱት ሕይወቱ ማለፉን  ጓደኛው ገልጿል፡፡

በወቅቱ ፖሊሶቹ ሲጠራሩ ስማቸውንና መልካቸውን ለይተዋቸው እንደነበር የገለጸው ይኸው የሟች ጓደኛ፣ ‹‹አንድ ግለሰብ ተደብድቦ እኛ ጋ ሲደርስ ሞቷል›› በማለት ክሊኒኩ ለፖሊስ ሪፖርት ሲያደርግ፣ አንደኛው ተጠርጣሪ  የሞተው ሌላ ሰው መስሎት በመምጣቱ መያዙን  ገልጿል።

የእሱን መያዝ ተከትሎ ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የ 27 ዓመት ወጣት የሆነው  ሟች ሀሚድ ወዳጆ  ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት መሆኑን ከቤተቦቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ከትናንት በስቲያ በፖሊስ ተደብድቦ መሞቱን መዘገባችን ይታወሳል በኢትዮጵያ ፤ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዘብ ተደርገው በሚቆጠሩት እንደ ፖሊስ ባሉት የፍትህ ተቋማት የሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ፤የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በቅርቡ ያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide