ፖሊስ በወልቃይት ኮሚቴዎች ላይ አንድ ምስክር ለማቅረብ የበጀት እጥረት ገጥሞኛል አለ

ሐምሌ ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ፖሊስ በሽብር ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ላይ በተደጋጋሚ ያልቀረበውን አንድ ምስክር አስሮ እንዲያቀርብ ታዞ የነበር ቢሆንም ምስክሩ የሚኖረው ትግራይ ክልል ውስጥ በመሆኑና በጀት ስላልተለቀቀልኝ ምስክሩን አስሮ የሚያመጣ አባል መላክ አልቻልኩም ሲል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መልሱን በደብዳቤ ገልፆአል።
አቃቤ ህግም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አጋጠመኝ የሚለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ምስክሩን ይዞ እንዲያቀር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆአል። በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እስር ቤት ከመሆናቸውም ባሻገር ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ምስክሩ ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ ለመመስከር የሚመጡትን ምስክሮች አልፈልጋቸውም ብሎ እያሰናበተ፣ የማይገኝና የሌለ ምስክር አመጣለሁ በማለት ደንበኞቻቸውን እያንገላታ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተውታል።” ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።
በአከባቢው የክልሉ ፖሊስ አለ። ፖሊስ ምስክሩን ማቅረብ ቢፈልገግ በቀላሉ ማቅረብ ይችላል ነበር።” ሲሉ ፖሊስ ሆን ብሎ በደንበኞቻቸው ላይ በደል እየፈፀመ እንደሆነ ገልፀዋል። አቃቤ ህግና ፖሊስ ቀጠሮ በማራዘም ደንበኞቻቸው ላይ የሰብአወዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ያሉት ጠበቆቹ ” የታሰረው ሰው ነው። ሰውን እስር ቤት አስቀምጠው ምስክሩን ለማቅረብ በጀት የለንም ማለት የተከሳሾችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው። የቀረበው ምክንያትም አሰማኝ ባለመሆኑ ምስክሩ ይታለፍ” የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የሰጠውን ምክንያት ታሳቢአድርጌያለሁ በሚል የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቶአል። እነ መብራቱ ለአራተኛ ጊዜ ለምስክር ተቀጥረው ምስክሩ ከመቅረቱም በተጨማሪ የዛሬው ቀጠሮ ለመጨረሻ እንዲሆንና ፖሊስ ምስክሩን አስሮ ማምጣት ካልቻለ ምስክሩ ታልፎ መዝገቡ ተመርምሮ ብይን ለመስጠት ሊቀጠር እንደነበር ጠበቃዎቹ ገልፀዋል። ምስክሩን ለመስማት ለነሀሴ 11/2009 አም ተቀጥሮአል።