ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ” የሚል መጽሀፍ ለሕትመት አበቁ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 28/2010)ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ” የሚል መጽሀፍ ለሕትመት አበቁ።

መጽሀፉ በኢትዮጵያ ሕዝብ አኗኗርና ህጸጾች ላይ እንዲሁም ባለፉትና በአሁኑ የአገዛዝ ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዝን ማስወገድና መንቀል ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ስርአት መተካት ካልቻለና የግፍ አዙሪቱ እንደሚቀጥል ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሀፋቸው ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አዲሱን መጽሀፋቸውን በተመለከተ ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

“እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ” የተባለው አዲሱ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መጽሀፍ በኢትዮጵያ ያሉ ወጣውረዶች ከመሻሻል ይልቅ ወደ ውድቀት ያመሩ መሆናቸውን ይገልጻል።

በኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ቁልቁል እየወረደ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአዲሱ መጽሀፋቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ካሳተሟቸው በርካታ መጽሀፍት አዲሱ እንዘጭ እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ የተባለው ስራቸው ከአገዛዞቹ ይልቅ በሕዝብ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ይናገራሉ።

በዚሁም የኢትዮጵያ ህዝብ በደል ያደረሱበትን አገዛዞች እያደፈጠ ቂሙን ለመወጣት ሲል ለሌላ አገዛዝ አሳልፎ በመስጠት ሕጋዊ ስርአት መፍተር አቅቶታል ብለዋል።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዝን ማስወገድና መንቀል ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ስርአት መተካት ካልቻለ የግፍ አዙሪቱ እንደሚቀጥል ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሀፋቸው ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቅርብ አመታት ውስጥ ብቻ የክህደት ቁልቁለት፣መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፣አዳፍኔና አሁን ደግሞ እንዘጭ እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ የሚሉትን መጽሀፍት አሳትመዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የአሁኑ መጽሀፋቸው እንዘጭ እንቦጭ የሚል ስያሜ ያገኘበትንም ምክንያት ይናገራሉ።

እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ የተባለው አዲሱ የፕሮፌሰር መስፍን መጽሃፍ በመጭው ቅዳሜ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሕዳር 11/2017 በአሜሪካ ቦስተን ከተማ ይመረቃል።

በመጽሀፉ ይዘት ላይም ሕዝብ በተሰበሰበበት ውይይት ይደረግበታል።

መጽሀፉም በመላው ኢትዮጵያ ወደፊት እንደሚሰራጭ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተናግረዋል።