ፕሬዚዳንት ኦቦንግ ኦሞድ ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቀ መምህራንም የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል

መጋቢት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፕሬዚዳንቱ ኦቦንግ ኦሞድ ስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ መምህራንም የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

 

ባለፉት ሳምንታት የመንግስትን ፖሊሲ ይቃወማሉ የተባሉ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን ተከትሎ ጋምቤላ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ መዘገባችን ይታወሳል። ከሳምንታት በሁዋላም ውጥረቱ በነበረበት መቀጠሉን ነው ዘጋቢያችን የገለጠው።

ሰሞኑን የኑዌርና የመዠንገር ተወላጆች የመሩት ስብሰባ በሶስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ተካሂዶ ነበር። በእነዚህ ስብሰባዎች ሁሉ ህብረተሰቡ መንግስት ከጥቃቱ ጀርባ እጁ አለበት በማለት ሲናገር ተደምጧል። በተለይም የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦሞድ ኦቦንግ በአስቸኳይ ስልጣናቸውን ካልለቀቁ ተጨማሪ ደም መፋሰስ ሊኖር እንደሚችል ተሰብሰባው ሲያስጠነቅቅ ሰንብቷል።

የፌደራሉ መንግስት አቶ ኦሞድን ለማውረድ መፈለጉ በግልጽ እየተንጸባረቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ይውረድ የሚል ተቃውሞ በሚያሰሙ ወገኖች ላይ ምንም እርምጃ ሊወሰድ አልፈለገም። አቶ ኦሞድን ለማውረድ መንግስት ፍላጎት ቦኖረውም ሁለት ነገሮች ግን እርምጃውን ከመውሰድ እንዳገዱት የአካባቢው ሰዎች ይነገራሉ። አንደኛው ምክንያት አቶ ኦሞድ በቅርቡ እኔ በዘር ማጥፋት የምጠየቅ ከሆነ ትእዛዙን የሰጠኝ መለስ ዜናዊም መጠየቅ አለበት በማለት የተናገረው ፣ ሌላ መዘዝ ይዞ ይመጣ ይሆናል የሚለው ፍርሀት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ግለሰቡ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ከመሬት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ሰንሰለት የገነባ በመሆኑ ችግሩ ሌላ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ በመፈራቱ ነው። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት መንግስት ህዝቡ ኦሞድ ይውረድ እያለ በይፋ በእየ ስብሰባ ቦታዎች እንዲናገር የፈቀደው፣ ኦሞድ በራሱ ጊዜ ስልጣኑን እንዲለቅ ለማግባባት ነው። እንደ ቅርብ ሰዎች እምነት ኦሞድ የስድስት ወር ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ስልጣኑን ሊያስረክብ ይችላል።

በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ያሰጋው መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱ በድንበር አካባቢ አሰሳ እንዲያካሂድ አዟል። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ የሰራዊት አባል ለአንድ ሳምንት ያክል ወደ ጫካ በመግባት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን አድኖ እንዲይዝ ወይም እንዲመታ ትእዛዝ ቢሰጠውም እስካሁን አልተሳካለትም። ከቅርብ ምንጮች በተገኘው መረጃ አማጽያኑ በቁጥር 300 እንደሚሆኑ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የአኝዋክ ተወላጆች ቢሆኑም ከመሀል አገር የመጡ ሰዎችም እንደሚገኙበት ታውቋል።

እስካሁን ድረስ ከአበቦ ወራደ የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ከሆኑት ከአቶ ኦቻ እና ከአንድ የቀበሌ ባለስልጣን በስተቀር በቅርቡ በ19 ሰዎች ላይ ለተፈጸመው ግድያ ምክንያት ናቸው የተባሉ ሰዎች አልተያዙም።

መንግስት ታጣቂዎቹ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ድጋፍ ያገኛሉ የሚል ጥርጣሬ ያለው ሲሆን ፣ በርካታ አምባሳደሮችና ከፍተኛ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች በአካባቢው ባለው የጸጥታ ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ትናንት ጋምቤላ ከተማ ገብተዋል። ውይይቱ የሚያተኩረው በሁለቱ ድንበሮች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን አድኖ ስለመያዝና ስለ ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ መምህራን ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ አድረገዋል። መምህራኑ አድማውን ያደረጉት የሁለት ወራት ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ነው። ክልሉ የ2004 ዓም በጀቱን ጨርሷል የሚል መልስ የተሰጣቸው መምህራን ትምህርት ቤቶችን ዘግተው ተማሪዎችን አሰናብተዋል። ተማሪዎችም ቅሬታቸውን በትምህርት ጽህፈት ቤት ፊት አሰምተዋል። ደሞዝ ያልተከፈላቸው መምህራን ብቻ ሳይሆኑ የክልሉ ፖሊስ አባላትና የጤና ሰራተኞች ናቸው። እነዚህ ወገኖችም በቅርቡ ተቃውሞ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎአል።

የክልሉ ባጀት ማለቁ ለመምህራን የተነገራቸው ሲሆን፣ በምክንያትነት የቀረበውም ክልሉ በቂ ገንዘብ ከታክስ ባለመሰብሰቡ ነው የሚል ነው።

ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት ግን የችግሩ ምንጭ አገራዊ ነው። መንግስት እየጨመረ የሚሄደውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ሲል ገንዘብ ማተም ማቆሙ ችግሩን ሳይፈጥረው አልቀረም። መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ገንዘብ በገፍ እያተመ ሰራተኛውን ሲከፍል በመቆየቱና፣ ከእንግዲህ ገንዘብ ማተም ግ በቱን የበለጠ የሚያባብሰው ሆኖ በማግኘቱ መካከል ባለ ቅራኔ የተፈጠረ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide