ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሽብርተኝነትን አስመልቶ ከናይጀሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንቶች ጋር ውይይት አደረጉ

ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንቶች ጋር በአህጉሪቱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚደረጉ ትብብሮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገለጸ።

ፕሬዚደንት ትራምፕ ከሁለቱ ሃገራት መሪዎች ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት አሜሪካ ሃገሪቱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት ድጋፍና ትብብር እንደሚደረግላቸው ቃል መግባታቸው ታውቋል።

በፕሬዚደንት ትራምፕ ከናይጀሪያው ፕሬዚደንት መሃሙድ ቡሃሪ ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ መግለጫን ያወጣው የናይጀሪያ ፕሬዚደንታዊ ጽ/ቤት ሁለቱ መረጃዎች በተለይ ሽበርተኝነትን ለመዋጋት በሚደረጉ ጥረቶች ዙሪያ መምከራቸውን እንደገለጸ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በዚሁ የስልክ ውይይት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከናይጀሪያ ጋር አዲስ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት እንደሚደረግ ቃል መግባታቸውን VOA እንግሊዝኛው ክፍል አቅርቧል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ የናይጀሪያ መንግስት ቦኮ ሃራም ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ሃይል ላይ እያካሄደ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ በማወደስ ዘመቻው የሃገራቸው ድጋፍ እንደማይለየው አስታውቀዋል።

የናይጀሪያው ፕሬዚደንት ቡሃሪ በዋሽንግተን ጉብኝትን እንዲያደርጉ ፕሬዚደንት ትራምፕ ግብዣ ማቅረባቸውም ታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚደንት የሁለቱ ሃገራት ትብብር በሚጠናከርበት ዙሪያ መምከራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና ዙማ በተለይ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መነጋገራቸው ተመልክቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ስልጣናቸውን በተረከቡ በቀናት ልዩነት ከግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ጋር የስልክ ውይይት ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።

ሁለቱ መሪዎች ባካሂዱት በዚሁ ውይይት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚቻሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ጊዜ ወስደው መነጋገራቸው በወቅቱ አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅት ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ለመዋጋት በሚካሄደው ዘመቻ የአሜሪካ ልዩ አጋር ተደርጋ መወሰዷ ሲነገር ቆይቷል።

አዲሱ የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር አዲስ የውጭ ፖሊሲዎችን ለመከተል መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካ ከባራክ ኦባማ አስተዳደር የተለየ የውጭ ፖሊስ እንደሚኖር የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በአሜሪካ የተደረገን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ከሃገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲቀጥልና ትኩረት ለማግኘት ከአንድ የማግባባት ስራ ከሚሰራ ድርጅት ጋር ለአንድ አመት የሚቆይ የ1.8 ሚሊዮን ዶላር ስምምንት መፈራረሙን መዘገባችን ይታወሳል።