ፍትህና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር አልኖርም በሚል ምክንያት አንድ መምህር ራሱን በእሳት አጋዬ

ህዳር 4 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በዋካ ከተማ ነዋሪ የሆነው መምህር የኔሰው ገብሬ   የስድስት ወረዳዎች ባለስልጣናት በአንድነት ተሰባስበው በቅርቡ በዋካ የተፈጠረውን ችግር በሚወያዩበት ወቅት፣  በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ እየተቃጠለ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገብቷል።

መምህሩ ራሱን እያነደደ ወደ ውስጥ ሲገባ የተመለከቱት የወረዳ ባለስልጣናት በመደናገጣቸው ከመምህሩ ለመራቅ ጥረት ያደርጉ ነበር ተብሎአል።

ምሁሩ በከተማው ውስጥ ከሚታወቁት በሳል ምሁራን መካከል አንዱ ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎቹ፣  “ፍትህ እና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር መኖር ሰልችቶኛል፣ በዚህ ሁኔታ በህይወት መቀጠል አዳጋች ነው” በማለት ይናገር እንደነበር ገልጠዋል።

መምህሩ በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ከስራ ተባሮ እንደነበር፣ በሁዋላም ወደ ስራ ለመመለስ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ እንዳልተሳካለት ታውቋል። በዋካ ከተማ ያለው ውጥረት አሁንም እንዳለ ሲሆን፣ በቅርቡ ለኢሳት መረጃ ሰጥተዋል ተብለው በጥርጣሬ የተያዙት ሰዎች አንዳንዶቹ በዋስ መለቃቀቸውም ታውቋል።

በአካባቢው የተሰማራው ልዩ ሀይል ግን አሁንም ከስፍራው አለመልቀቁን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በዋካ ከተማ ከወረዳና መብት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ “የህዝቡ ጥያቄ ፍትሐዊ ቢሆንም፣ መንግስት ግን አስፈላጊውን መልስ ሊሰጥ አልቻለም” በሚል ምክንያት፣ የቶጫ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ፈቃዱ ወልደሩፋኤልና  ፣ የዞኑ አቃቢ ህግ የሆኑት አቶ ከበደ ካሳ በራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።