ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ በጸረ ህዝቦች ግፊት ሚኒስትሮችን እንከስም አሉ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 24/2009)በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ፓርላማ በዚህ ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ተነገረ ።
ፓርላማው የሚሰበሰበው በቅርቡ የሚጠናቀቀውን የአሰቸኳይ አዋጅ የተመለከተ ይሁን በሙሰና የተጠረጠረ ከፍትኛ ባለስልጣን ለማይዝ ገና የታወቀ ነገር የለም።
በሙስና የተከሰሱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን መንግስት ቢያሳውቅም ከፍተኛ ባለስልጣን ከሚላቸው እስካሁን የታሰረ አለመኖሩ ይታወቃል።
ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ በጸረ ህዝቦች ግፊት ሚኒስትሮችን አናስርም ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።
እረፍት ላይ ለሚገኙት የፓርላማ አባላት የቀረበው ጥሪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለመምከር የሚል ምክንያት ተቀምጧል።
ጥሪው ግን ከወቅቱ የሙስና ርምጃ ጋር በተያያዘ የአንዳንዶች ያለመከሰስ መብት ሊነሳ ይችላል የሚለው ጥርጣሬ እንዲንጸባረቅ አድርጓል።
በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሙስና ርምጃ ተወስዷል በሚል ሲገለጽ የቆየው ዘገባ ካስከተለው ትችት ጋር በተያያዘ የፓርቲና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎችና የመንግስት ሰራተኞች በሚል ዘገባዎቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
ሆኖም ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ከፍተኛ ባለስልጣን የሚባሉት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች አይደሉም በማለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በግፊት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎችን እንዲሁም ምክትል ሚኒስትሮችን እንከስም ያሉት አቶ ጌታቸው አምባዬ እነዚህ የስራ ሃላፊዎች ከሙስና ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ነገር የለም በማለት ርምጃው ስር ስሩ ላይ ያተኮረ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከአመታት በፊት የታሰሩት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ በሚኒስትር ማእረግ ላይ የነበሩ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሲልም በህወሃት ክፍፍል ወቅት የታሰሩት አቶ ስዬ አብርሃ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
የመጀመሪያ የሚባለው የሙስና ርምጃ የተወሰደባቸው አቶ ታምራት ላይኔም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ላይ እያሉ መታሰራቸው ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ በማለት በቅድሚያ መግለጫ ሲሰጡ ባከነ የተባለው ገንዘብም ከ2 ቢሊየን ብር በታች መሆኑን ገልጸው ነበር።
ተጨማሪ 4 ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ተዘረፈ ወይንም ባከነ የተባለው ገንዘብ መጠን 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መድረሱን ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሌብነት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል ተብለው ከተዘረዘሩት የመንግስት ተቋማት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ በማባከን በቀዳሚነት የተጠቀሰው የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ሲሆን ዝቅተኛ ሆኖ የተመዘገበው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት እንደሆነም ተመልክቷል።
ባከነ ተብሎ የተጠቀሰው 41 ሚሊየን ብር ነው።
ቀጥሎ በዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጠው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሲሆን በ198 ሚሊየን ብር ብክነት ተጠያቂ መሆኑም ታውቋል።
በ198 ሚሊየን ብር ብክነት ተጠያቂ የሆነው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ፈቃዱ ሃይሌ ሲታሰሩ ከ1 ቢሊየን 4 መቶ ሚሊየን ብር በላይ የተዘረፈው ወይንም ባከነበት የተባለው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊዎች ግን በሙስና ተጠያቂ አልሆኑም።
የቀድሞው ስራ አስኪያጅ አቶ ዛኢድ ወልደገብርኤል እንዲሁም የአሁኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አርአያ ግርማይ የህወሃት አባላት በመሆናቸው እንዳልተጠየቁ በታዛቢዎች ዘንድ ታምኖበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ሰኔ 20/2009 እረፍት የወጣው ፓርላማ በዚህ ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል።
ፓርላማው የተጠራው በቅርቡ የሚያበቃውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ እንዲሆነ ለፓርላማ አባላቱ ተነግሯቸዋል።
ሆኖም ግን የአንዳንድ የፓርላማ አባላት ያለመከሰስ መብት ሊነሳ ይችላል የሚለው ጥርጣሬ እያየለ መጥቷል።