ግብፅ ሱዳንና ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በባለሙያዎች ደረጃ ሲያካሄዱ የነበረው ውይይት ባለመግባባት ተበተነ

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ለ14ኛ ጊዜ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በባለሙያዎች ደረጃ ሲያካሄዱ የነበረው ውይይት ባለመግባባት ተበተነ።

የሶስቱ ሃገራት ተወካዮች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ በሚኖረው ተፅዕኖ ዙሪያ በአዲስ አበባ በመሰባሰብ የሁለት ቀን ምክክር ቢያደርጉም፣ 14ኛ ዙር ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁን የግብፅ ባለስልጣናት ይፋ ማደረጋቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር የተሰኘ ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ግድቡ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በገለልተኛ የባለሙያ ቡድን በማስጠናት ላይ ቢሆኑም፣ በተናጠል የጋራ ውይይት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የግብፅ የመስኖ ሚኒስቴር ለአለመግባባት የተነሱባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ለመምከር መድረክ እንደሚዘጋጅ የገለጸ ሲሆን፣ መቼና የት ሊካሄድ እንደሚችል ግን ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሁለት የፋይናንስ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በማጥናት ላይ ሲሆኑ የጥናታቸውን ውጤት ከስድስት ወር በኋላ ለሶስቱ ሃገራት መንግስታት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፈረንሳዮቹ ኩባንያዎች ለሃገሪቱ የሚያቀርቡት የጥናት ውጤቶች ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ባለፈው አመት ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

የግብፅ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል በዩጋንዳ በኩል አዲስ የመወያያ መድረክ እንዲካሄድ ጥያቄን አቅርቦ የሚገኝ ሲሆን፣ ዩጋንዳ የተፋሰሱ ሃገራት በግብፅ ሃሳብ ላይ እንዲመክሩ ጥሪ ማቅረቧ ታውቋል። ይሁንና ኢትዮጵያ በግብፅ የቀረበውን ሃሳብ ለመመልከት በቂ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት በተያዘው ወር ሊካሄድ የነበረው መድረክ ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቃለች።

ይኸው አዲስ ውይይት በቀጣዩ ወር አጋማሽ በዩጋንዳ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ግብፅ በወንዙ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስከበር አጀንዳ መያዟ ተመልክቷል።

ሃገሪቱ በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ በወንዙ ፍሰት ላይ ተፅዕኖን ያሳደራል በማለት ስጋቷን በመግለጽ ላይ ብትሆንም፣ ኢትዮጵያ ግድቡ የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖርም ስትል ምላሽን ስትሰጥ ቆይታለች።