ግልገል ጊቤ ሶስተኛው የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት የቱርካና ሃይቅ ላይ የውሃ መበከልን ሊያስከተል ይችላል ሲል የኬንያ መንግስት ቅሬታን አቀረበ

ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)

የኬንያ መንግስት በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የጀመረው ግልገል ጊቤ ሶስተኛው የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት በአካባቢው በሚገኘው የቱርካና ሃይቅ ላይ የውሃ መበከልን ሊያስከተል ይችላል ሲል ቅሬታን አቀረበ።

የሃገሪቱ የአካባቢ ሚኒስትር የሆኑት ጁዲ ዋኩንጉ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑት የተፈጥቶ ሃብቶች ጥቅም ላይ በሚውሉ ጊዜ አለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ያደረገ ስምምነት ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት መግለጻቸውን ዲይሊ ኔሽን ጋዜጣ አርብ ዘግቧል።

በተያዘው ሳምንት ሂውማን ራይትስ ዎች በሃይል ማመንጫው ፕሮጄክት ዙሪያ በመካሄድ ላይ ያሉ የመስኖ ስራዎች የቱርካና ሃይቅ እንዲደርቅ እያደረጉ መሆኑን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።

በዚሁ የሃይል መመንጫ ፕሮጄክት በስፍራው የሚኖሩ ግማሽ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን በወንዙ ላይ የተመሰረተው የኑሮ እንቅስቃሲያቸው አደጋ ውስጥ ገብቶ እንደሚገኝ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አመልክቷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ያጣውን ይህንኑ ሪፖርት ተከትሎ የኬንያ ባለስልጣናት ተመሳሳይ ስጋት ማሰማት የጀመሩ ሲሆን፣ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቱ በተለይ የውሃ ብክለትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን የኬንያ ባለስልጣናት ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ሃብቶች ጥቅም ላይ በሚውሉ ጊዜ የሌላኛውን ሃገር መጉዳት በሌለበት ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት የኬንያው የአካባቢ ካቢኔት ሴክሬታሪ ( ሚኒስትር) የሆኑት ጁዲዋኩንጉ ገልጽዋል።

ሃላፊዋ የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ዙሪያ እያካሄደ ያለው ሁለገብ የመስኖ ስራ በቱርካና ወንዝ ላይ ብክለትን ያስከትላል የሚል ስጋት እንዳሳደረ ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ተናግረዋል።

ፕሮጄክቱ የሚያመጣው ተፅዕኖ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለው አስረድተዋል። በአካባቢ የተጀመረውን ይህንኑ ግንባታ ተከትሎ ካለፈው አመት ጀመሩ የቱርካና ሃይቅ በ1.5 ሜትር የውሃ ከፍታው መቀነሱንም ሂውማን ራይትስ ዎች የአሜሪካ የግብርና መምሪያ መረጃን ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አስፍሯል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ከኬንያ መንግስት ጋር ምክክር እየተካሄደበት የተሰራ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል።

በፕሮጄክቱ ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶች ዕልባት ለመስጠትም ሁለቱ ሃገራት መደበኛ የሆነ ምክክር ሲያካሄዱ መቆየታቸው ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በሰጡት ማስተባበያ ገልጸዋል።

የኬንያ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች በሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቱ ምክንያት በሁለቱ የድንበር ዙሪያ የሚኖሩ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አመልክቷል።

በወንዙ ዙሪያ የሚኖሩ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች በበኩላቸው በእርሻና አሳ ማስገር ላይ የተመሰረተው ህይወታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጎዳት በጀመሩ ለምግብ እጥረት እየተጋለጡ መሆኗቸው ለሂውማን ራይስት ዎች ይገልጻሉ።