ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንዔል ሺበሺ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረቡ

ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2009)

ላለፉት አምስት ወራት ያለምንም የክስ ሂደት በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና የቀድሞ የአንድነት አመራር አቶ ዳንዔል ሺበሺ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረቡ።

በቦሌ ክ/ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ አቤቱታ አቅራቢዎች በጥቅምት ወር በሃገሪቱ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

በማህበራዊ ድረገጾች የተለያዩ ጽሁፎችን ሲያቀርቡ የነበሩት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንዔል ሺበሺ መቀመጫቸውን በውጭ ካደረጉ በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ አካላት ጋር ግንኙነት ኣላቸው የሚል ምክንያት ቀርቦባቸዋል።

ይሁንና ፖሊስ ሁለቱ አቤቱታ አቅራቢዎችን እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አላቀረበም። ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ  ባቀረቡት ደብዳቤ ከእስር የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

ባለፈው ወር በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንዔል ሺበሺን በምን አይነት ሁኔታ ማቆየት እንዳለበት ግራ መጋባቱን ገልጾ እንደነበርም ይታወሳል።

ፖሊስ ጣቢያው ያቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንዔል ሺበሺ ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ቢወሰዱም ታሳሪዎቹ ጉዳያቸው ገና የሚታይ ነው በማለት በፖሊስ ጣቢያው እንዲቆዩ አድርጓል።

ይሁንና አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከአምስት ወር የእስር ቆይታ በኋላም ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ስጋት እንዳደረባቸው ይገልጻሉ ይገልጻሉ።

ከሁለቱ ታሳሪዎች ጋር ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ በተመሳሳይ ሁኔታ ለእስር ተዳርጎ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ ያለምንም ክስ ከእስር መለቀቁ የሚታወስ ነው።

በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከ24ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለእስር ተዳርገው እንደነበር አይዘነጋም።

ከታሳሪዎቹ መካከል ወደ 5ሺ አካባቢ የሚጠጉት በሃገሪቱ ከተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

ይሁንና ለወራት ያህል በእስር ላይ የሚገኙት ሰዎች መቼ ክሱ እንደሚመሰረትባቸው የተገለጸ ነገር የለም።