ዶ/ር መረራ ጉዲና የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው

የካቲት ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ፕሬዚደንት ዶ/ር መረራ ጉዲና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር ሙሃመድ፣ ኢሳት እና ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሌሉበት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል። በአውሮፓ ኅብረት ግብዣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ምስክርነት ለመስጠት ቤልጅየም በመገኘት ንግግር አድርገው ሲመለሱ ህዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር ከመኖሪያ ቤታቸው በደኅንነት ኃይሎች ታፍነው የተወሰዱት ዶ/ር መረራ፣ የአርበኞች ግንቦት7 የተባለውን የሽብር ቡድን ተልእኮ ለማሳካት በማሰብ ከ2008 ዓም ጀምሮ የሁከትና ብጥብጥ ጥሪ በማስተላለፍ እንዲሁም በአንዳንድ የኦሮምያ እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ህብረተሰቡ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገባ በማድረግ በመቀስቀስና አመራር በመስጠት በተነሳው ሁከት ምክንያት በአማራ ክልል፣ በደቡብባ በሰሜን ጎንደር እና በባህርዳር ዙሪያ የመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች ንብረት እንዲወድም ፣ መሰረተ ልማት እንዲቋረጥ፣ ሰው እንዲሞት፣ በሰው አካል ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።