ዶ/ር መረራ ጉዲና በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ የአውሮፓ ህብረት ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2009)

የአውሮፓ ህብረት በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና የተመሰረተባቸው ክስ ውድቅ ተደርጎ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ጥሪ ቀረበ።

በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሪፖርትን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የአውሮፓ ፓርላማ በሃገሪቱና በኦሮሚያ ክልል ከተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግድያ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት አሳስቧል።

በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከወራት በፊት በህብረቱ ፓርላማ ግብዣ ተደርጎላቸው ከተመለሱ በኋላ በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። 

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሩን መታሰር ተከትሎ ስጋቱን ሲገልፅ የቆየው ፓርላማ ዶ/ር መረራ ጉዲና በከሳሽ አቃቤ ህግ የተመሰረተባቸው ክስ ውድቅ ተደርጎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ሲል ጥያቄውን ለመንግስት አቅርቧል።

የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ ዶ/ር መረራ ጉዲና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈዋል በማለት ክስ መስርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ የኦፌኮ አመራር የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያው ጸረ ሽብር ህግ ሃሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹ የፖለቲካ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ለማሰር እየዋለ እንደሚገኝም አክሎ አብራርቷል።

መንግስት የሃገሪቱ ዜጎች በተለያዩ መንገደኞች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልፁ ጥሎ የሚገኘውን እገዳም እንዲያነሳ ፓርላማው በመግለጫው አመልክቷል።

በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ሲካሄድ ከቆየውው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ፓርላማው አውስቷል።

የአውሮፓ ፓርላማ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሃገሪቱ በጸጥታ ሃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎችና የጅምላ እስራቶች በገለልተኛ አካል መጣራት እንዲካሄደበት በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ መንግስት ተባባሪ እንደማይሆን ምላሽን ሰጥቷል።

መንግስታዊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አካሄጀዋለሁ ባለው ምርመራው 745 ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጽም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር በመንግስት ከተገለጸው ሊበልጥ እንደሚችል አስታውቀዋል።

ገለልተኛ ምርመራን እንዲያካሄድ የተከለከለው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በመንግስት ይፋ ለተደረገው ሪፖርት ዕውቅናን እንደማይሰጥ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

ይሁንና የራሱን ምርመራ ለማካሄድ ኮሚሽኑ ጥያቄውን በድጋሚ አቅርቧል።

የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ባለው የሰብኣዊ መብት ከገለጸው ስጋቱ በተጨማሪ የደቡብ ሱዳንና የዛምቢያ መንግስትም ለእስር ተዳርገው የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።