ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ቧንቧ መስመር ለመዘርጋት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተፈራረመች

የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጅቡቲ ወደብ በኩል ነዳጅ ለዉጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላትን የቧንቧ መስመር በኢትዮጵያ ለመዘርጋት ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ተዘግቧል።

የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ለአሶስየትድ ፕሬስ የዜና አገልግሎት እንደገለፁት የቧንቧ መስመሩ ባለቤት ደቡብ ሱዳን እንደምትሆንና መስመሩ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ጅቡቲ የሚተላለፍበት ተጨማሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሁለቱ መንግስታት ባለስልጣኖች በወሩ መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ላይ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን የቻይና፤ የአሜሪካንና የአዉሮፓ ኩባንያዎች የቧንቧ መስመሩን የቅድሚያ ጥናት ለመስራትና ግንባታዉን ለማካሄድ ፍላጎት ማሳየታቸዉን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በእንዱስትሪዉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ግንባታዉ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅና ከሶስት አመት በላይ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል። በኬንያ ጠረፍ በኩል ሌላ መስመር ለመዘርጋት የተደረገዉንም ስምምነት ተችተዋል።   

በቅርቡ ነፃነቷን የተቀዳጀችዉ ደቡብ ሱዳን ነዳጁን አጣርታ ወደ ዉጭ ገበያ ለማቅረብ ሁዋላ ቀር የሆነዉ የመሰረተ ልማት ደረጃዋ አልፈቀደላትም።

በሌላ በኩል ሱዳን በቂ መሰረተ ልማት የዘረጋችና በቀይ ባህር በኩል በቀላሉ ለዉጭ ገበያ የማቅረቢያ ተርሚናል ባለቤት ብትሆንም ደቡብ ሱዳን በኪራይ ልትጠቀም በምትችልበት ሂሳብ ላይ መግባባት አልቻሉም።  

የካርቱም መንግሰት 815 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድፍድፍ ነዳጅ እንደሰረቀና ህገወጥ የቧንቧ መስመር በመዘርጋት በድብቅ ለመዉሰድ እንደተዘጋጀች ደቡብ ሱዳን ትከሳለች።

በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረዉ አለመግባባት ፣  ደቡብ ሱዳን ምንም እንኳ 98 በመቶ የሚሆነዉ የአገሪቱ ገቢ በነዳጅ ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም፣  ካለፈዉ ወር ጀምሮ ነዳጅ የማምረት ተግባሯን እንዳቆመች አስታዉቃለች።

የደቡብ ሱዳን ውሳኔ የሰሜን ሱዳንን መንግስት ያስቆጣ ይሆን ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አንድ የሱዳን ባለስልጣን አማራጭ አለን ካሉ እስየው ብለው መልሰዋል።

የደቡብ ሱዳን ውሳኔ የአካባቢውን አገሮች ወደ ግጭት ሊወስዳቸው እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ። ባለፈው ሳምንት አቶ መለስ ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን ጋር እንድትስማማ ለማድረግ ያቀረቡት ሀሳብ ውድቅ እንደተደረገባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

ደቡብ ሱዳን በአቶ መለስ የቀረበውን ሀሳብ ነዳጅን ብቻ ያካተተና ድንበርንና የአቤይ ግዛትን ከስምምነት ያወጣ ነው በሚል ምክንያት ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

ደቡብ ሱዳን  በኢትዮጵያ በኩል አልፎ ጅቡቲ  የሚደርስ የነዳጅ መስመር እዘረጋለሁ ማለቷ ፣ ለአልበሽር መንግስት የሚዋጥ እንደማይሆንና ሰሞኑን ጦርነት አይቀሬ ነው በማለት የተናገሩትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥሩ ምክንያት እንደፈጠረላቸው ተንታኞች ያክላሉ።