ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ላይ በመጻፉ በአሸባሪነት መከሰሱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አወገዘ

ግንቦት ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዮናታን ተስፋዬ መንግስትን በመተቸቱ ብቻ በሽብር ክስ መከሰሱን አውግዟል። ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የተነሳውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ የመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከቅም በላይ ሃይል መጠቀማቸውን በማህበራዊ ድረገጾች ማውገዙ ሊያስከስሰው አይገባም ብሏል።
ወጣት ዮናታን ተስፋዬ በአንድ ወቅት ”ሰላማዊ የሆነ ውይይት ማድረግ ሲቻል በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ ለምን አስፈለገ?” ሲል ገዥውን ፓርቲ ኮንኗል።
ዮናታን “የመጻፍና የመናገር መብት አለኝ” በማለት የመከላከያ መልስ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ግን አልተቀበለውም። የመሃል ዳኛው በላይሁን አወል ”የመጻፍ እና መናገር መብትን በመጠቀም ሽብርተኝነት እንዲሰፍን አድርጓል።” በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፈዋል።
”ዮናታን መጻፉ ወንጀል አይደለም። ቢሆንም በዚህ አፋኝ እና ህጋዊነት በሌለው የሽብር ሕግ መሰረት ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ ይችላል። ጋዜጠኞችና ሕጋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስትን እንዳይተቹ የማድረግ ስራዎች በገዥው ፓርቲ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ሲሉ በምስራቅ አፍሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምክትል ዳሬክተር ሚካኤል ካጋሪ ተናግረዋል። ወ/ሮ ካጋሪ ”የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ለማፈን የሚጠቀምበት አሰራር አሳፋሪና የሕግን ልእልና ማዋረድ ነው።” ሲሉም ኮንነዋል።
ከዓመት በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ የለውጥ ንቅናቄ ከ669 በላይ ንጹሃን ዜጎች በጸጥታ ሃይሎች በግፍ ተገለዋል።