ያለፈው የፈረንጆች አመት ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ የገባችበትና በ10ሺ የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎችም ለእስር ተዳርገው የነበረበት ነበር ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

ኢሳት (ጥር 5 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2016 አም የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ የገባችበትና በ10ሺ የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎችም ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው ሂውማን ራይስት ዎች አስታወቀ።

በአለም ዙሪያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች የ2017 አም ሪፖርቱን ያወጣው የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አፈናና ረገጣ ከመቼው ጊዜ በላይ የከፋ ሆኖ መቀጠሉን ገልጿል።

ባለፈው አመት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ለተወሰኑ ጥያቄዎች ምላሽን ከመስጠት ይልቅ የሃይል ዕርምጃን ሲወስድ መቆየቱን ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር ሲባል በጥቅምት ወር የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።

የሟች ቤተሰቦች፣ ከእስር የተለቀቁና ሌሎች አካላትን ዋቢ በማድረግ ሪፖርቱን ያጠናከረው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በቅርቡ ከእስር የተለቀቁ በርካታ ሰዎች በእስር ቤት ቆይታቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ማረጋገጣቸውንም አመልክቷል።

በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገደሉም መንግስት ድርጊቱ እንዲጣራ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል መቅረቱንም ሂውማን ራይትስ አውስቷል።

በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የጥራት ባለሙያ (ተመራማሪ) የሆኑት ፊሊክስ ሆንር (Felix Horne) መንግስት በተደጋጋሚ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ተግባራዊ እንደሚያደርግ እየገባ ያለው ቃል በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።

በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት እና ህዝባዊ ጥያቄ ትርጉም ያለው ምላሽን ካላገኘ ችግሩ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

በአለም ዙርያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ባለ 687 ገጽ 27ኛ እትሙን ይፋ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች ከህዝባዊ ተቃውሞው በፊት ቢሆንም በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ጋዜጠኞችንና ሌሎች አካላትን ያነጣጠረ ስልታዊ አፈና ሲካሄድ መቆየቱን አክሎ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም ከ10 የሚበልጡ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ የፓርቲ አባላትና በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ እስር ቤቶች እየተንገላቱ እንደሚገኝ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣትን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

ይሁንና ስለተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት አዋጁ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ሊውል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች የሚያስተባብለው ( የሚያጣጥለው) መንግስት ሃሙስ ይፋ ስለተደረገው ሪፖርት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ይገልጻሉ።