የ2019 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል ተባለ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/2010) የ2019 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀምር ታወቀ።

ብሪታኒያ፣ካናዳና ቻይናን ጨምሮ ከ20 የሚበልጡ ሀገራት ዜጎች በእድሉ እንዳይጠቀሙ ዕገዳ ተጥሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነውና ከቀደመው የቀጠለው ፕሮግራም ከአፍሪካ ናይጄሪያን አስቀርቷል።

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መስከረም 23/2010 በዋሽንግተን ዲሲ ሰአት አቆጣጥር እኩለ ቀን ላይ የሚጀምረው ፕሮግራም እስከ ጥቅምት 28/2010 ድረስ እንደሚቀጥልም ታውቋል።

በ2019 የዲቪ ሎተሪ የማይሳተፉ ወይንም ተቀባይነት የሌላቸው ሀገራትም ዝርዝር ይፋ ሆኗል።

በዚህ ዕገዳ ውስጥ 50ሺህና ከዚያ በላይ ዜጎቻቸው በአሜሪካ የሚኖሩ ሀገራት በዲቪ ሎተሪው እንዳይሳተፉ ክልከላ ተደርጎባቸዋል።

የካናዳ፣የቻይናና የብሪታኒያ ዜጎችም በክልከላው ውስጥ ተካተዋል።ከአፍሪካ ሀገራትም በዚህ አመት የዲቪ ሎተሪ ናይጄሪያውያን እንደማይሳተፉ ከወጣው ዝርዝር መረዳት ተችሏል።

ከቻይና፣ብሪታኒያ፣ካናዳ፣ናይጄሪያና ባንግላዴሽ በተጨማሪ ብራዚል፣ኮሎምቢያ፣ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ኤልሳልቫዶር፣ጓቲማላ፣ሔይቲ፣ሕንድ፣ጃማይካ።ሜክሲኮ፣ፓኪስታን፣ፊሊፒንስ፣ፔሩ፣ፖላንድ፣ደቡብ ኮሪያና ቬትናም በ2019ኙ የዲቪ ሎተሪ እንደማይሳተፉ የአሜሪካ መንግስት እገዳ ጥሏል።

ሀገራቱ ባለፉት 5 አመታት ብቻ ከ50 ሺ ሰው በላይ በሕጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ በማስገባታቸው ከእድሉ መሰረዛቸው ተመልክቷል።