የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ስራ መሰማራት የንግድ እንቅስቃሴውን እያደከመው ነው ተባለ

ሰኔ 15/ 2009

የፓለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ሥራ ውስጥ መሰማራታቸው የንግድ እንቅስቃሴውን እያዳከመው መሆኑን ታዋቂው የንግድ ሰው ገለፁ።

በህወሓት በግል ንብረትነት የሚታወቀው ሬዲዮ ፋና “የፌደራል ስርዓት ግንባታን፣ ብዝሃነትን የጋራ ተጠቃሚነትን የማስተናገድ አቅም” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት ታዋቂው የንግድ ሰው አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ የፓርቲ ኩባንያዎች በግለሰብ ሥም ጭምር እየተደራጁ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። 

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ እንዳሉት ፌደራላዊ ስርአት በኢትዮጵያ መመስረቱ በራሱ ችግር አይደለም። ከፌደራል ስርአት አወቃቀር ጋርም ችግር የለብኝም ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሁኔታ በኪራይ ሰብሳቢነት ማሳበቡና ማሳነሱም ተገቢ እንዳልሆነ ግን አመልክተዋል። ችግሩ የተከሰተው በፌዴራል ስርዓቱም ውስጥ ሆነን ለመቻቻልም፣ ለማዳመጥም የስርዓት አሰራር ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።

ትናንትን በመካድ ወይንም እንዳልነበረ በመቁጠር በደርግ የተጀመረው ሁኔታ ዛሬ ተባብሶ በመቀጠሉ እንደጀግና የምንመለከታቸው ሰዎችና ተግባራትን ኣጥተናል በማለት ይህም አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የመድረኩ አወያዮች ወደ እለቱ አጀንዳ እንዲመለሱ የጠየቁዋቸው የቀድሞው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ የንግድ ም/ቤቶች ፕሬዝዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በችግርነት የሚነሳው የአፈጻጸም ችግር ከስርአቱ እንደሚመነጭ ማሳያዎችን አንስተዋል።

ሹመትን እንደ እውቀት የሚወስዱ ባሉበት ከችሎታ ይልቅ ታማኝነት ቅድሚያ ሲሰጠው የአሰራር ችግር እንደሚመጣ አይታወቅም ነበር ወይ? በማለትም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የማይሆኑ ሕጎች ይጻፋሉ በማለት የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 39 ጠቅሰው የተንደረደሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በህገመንግስቱ መገንጠል እንደማይተገበር እየታወቀ እንደተጻፈው ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ውስጥ አይሰማሩም ተብሎ በህግ የተቀመጠውም፣ በተግባር አለመዋሉን ይልቁንም ትልልቆቹ ነጋዴዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህም አባላቶቻቸውን ይደጉሙበታል ብለዋል።

ይህንን አንዳንዶች የሃብት ዝውውር በማለት እንደሚገልጹት ያስታወሱት ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ  በግለሰብ ነጋዴ ስም ጭምር የፓርቲ ኩባንያዎች መኖራቸውን ርሳቸው በሚሰሩበት የፋይናንስ ዘርፍ  በግልጽ የሚታይ መሆኑንም በዝርዝር ተመልክተዋል።

“በሰራተኞች የስራ ስምሪት ረገድ ማነው ይበልጥ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆነው እነማንስ ናቸው የተገፉት? ይህ በየብሄረሰቡ ተጠንቷልን? በማለት የጠየቁት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በግልጽ እንነጋገር ፥ አንተፋፈር ሲሉም ተደምጠዋል። ጠባብነትንና ትምክህት ችግር ናቸው እየተባለ እራሳችን እዛ ውስጥ መገኘታችንስ እንዴት ይታያል ሲሉም ጠይቀዋል።