የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የቀብር ስነ-ስርዓት በአዲስ አበባ መንበረ-ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

ኢሳት (የካቲት 14 ፥ 2009)

ከቀናት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የቀብር ስነ-ስርዓት ማክሰኞ በአዲስ አበባ መንበረ-ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም አመታት ጥናትና ምርምር በማካሄድ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ፓንክረስት ከአራት ቀናት በፊት በ90 አመታቸው በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የፕሮፌሰር ፓንክረስት ቤተሰቦች ወዳጆችና የስራ ባልደርቦች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀብር ስነስርዓቱ መታደማቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በኢትዮጵያ መኖር የጀመሩት የታሪክ ምሁሩና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ 22 መጽሃፎችንና 400 የሚደርሱ ፅሁፎችን ለአለም አቀፍ መጽሄት ማበርከታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።

የአክሱም ሃውልት ከጣሊያን እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋጽዖን ያደረጉት ፕሮፌሰር ፓንክረስት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ50 አመት በላይ የሰጡት ምሁራዊ አስተዋጽዖ ዩኒቨርስቲው ዛሬ ለደረሰበት እድገት የማይረሳ ሚና ማኖራቸውን የቅርብ የስራ ባልደርቦቻቸው ይገልጻሉ።

የታሪክ ምሁሩ በርካታ አመታት ላደረጉት የታሪክ አስተዋጽዖ ከአጼ ሃይለስላሴ ሽልማት ድርጅቶችና ከእንግሊዝ መንግስት የወርቅ ሜዳሊያና ኒሻን ለመሸለም እንደበቁም የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ እናት ሲልቪያ ፓንክረስት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ከአመታት በፊት መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል።