የፓርላማው ቃል አቀባይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለምን እንደተጠሩ አላውቅም አሉ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 20/2009)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የፊታችን አርብ ሐምሌ 28/2009 አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱን የፓርላማው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ገለጹ።
ሆኖም ፓርላማው ለምን እንደተጠራ የፓርላማው ቃል አቀባይ እንደማያውቁ በሐገር ቤት ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፓርላማው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አጸደ ረጋሳ ፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን አረጋግጠዋል።
ሆኖም ፓርላማው ለምን እንደተጠራ እንደማያውቁ አመልክተዋል።
አንዳንድ የገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ጥሪው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ እንደሆነ ቢገልጹም ሊሎች ምንጮች ግን ጥሪው ይበልጥ ከሙስና ክሱ ጋር በተያያዘ የተጠርጣሪዎችን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
መስከረም 28 2009 ለወራት የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መጋቢት 28 ሲያበቃ በተወሰኑ ማሻሻያዎች ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ ይታወሳል።
የማራዘሚያው አዋጅ ሐምሌ 28/2009 ስለሚያበቃ ፓርላማው ለአርብ ሐምሌ 28/2009 የተጠራው ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ቢገመትም ተጨማሪ ሌሎች አጀንዳዎች እንደሚኖሩም ታምኖበታል።
በሌላም በኩል ፓርላማው የተጠራው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ አይደለም በማለት ጥርጣሬያቸውን የሚገልጹት ወገኖች ደግሞ ዋናው ጉዳይ እሱ ቢሆን ኖሮ ፓርላማው ሰኔ 30 ከመነሳቱ በፊት አስቀድሞ ማራዘም ይቻል እንደነበር ይገልጻሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ሲራዘም ቀነ ገደቡ ከማለቁ ከሳምንት በፊት መጋቢት 21/2009 እንደነበር በማስታወስም ለአባባላቸው ማጠናከሪያነት ይጠቅሱታል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መስከረም 28/2009 አውጆ ተግባራዊ ካደረገ ከሳምንታት በኋላ ፓርላማው ተሰብስቦ እንዳጸደቀው በማስታወስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት አዋጁን ማራዘም አይቻልም ወይ ሲሉ ይጠቅሳሉ።
የህገወጥነት ጥያቄ የሚያስነሳም ከሆነ ሲጀመር ለምን ህገወጥ ድርጊት ተፈጸመ የሚለውን በማነጻጸሪያነት ያነሳሉ።
ከነዚህም ሁኔታዎች በመነሳት በመሃልና በመጨረሻ ሁኔታዎች ካልተለዋወጡ ፓርላማው የተጠራበት ልዩ ስብሰባ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይልቅ ከሙስና ክሱ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚለው ትኩረት የሳበ ሆኖ ተገኝቷል።
በፓርላማው ወንበር ያላቸው ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት ያላቸው በመሆኑ በፓርላማው ይህ መብታቸው ካልተገደበ በወንጀል እንደማይጠየቁ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ፓርላማው በአስቸኳይ ስብሰባው በተጨማሪነት ከሚያነሳቸው አጀንዳዎች አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከተ እንደሆነ የሚገልጹት ምንጮች በዚህም አስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደማይነሳና በጥቂት ማሻሻያዎች እንደሚቀጥል ገልጸዋል።