የፌዴራል አቃቤ ህግ ዶ/ር መረራ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ባለመቀበል ለፍ/ቤት አቤቱታ አቀረበ

ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ አቃቢያን ሕግ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ እንደማይቀበሉት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ። 

የፌደራል አቃቤ ሕጎች ማክሰኞ ሰኔ 13/ 2009 ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የተቃውሞ አቤቱታ ዶ/ር መረራ ጉዲና ክሳቸው ከኢሳትና ኦኤምኤን ተለይቶ የሽብር ክሳቸው በሌላ መታየቱን እንደማይቀበሉ ገልፀዋል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በአቃቤ ሕግ የቀረበውን በርካታ ክሶች ከሽብርተኛ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም በሚል በጠበቆቻቸው አማካኝነት ከአንድ ወር በፊት ተቃውመው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር።

ስለዚህም በእሳቸው ላይ የቀረበው ክስ ከኢሳትና ከኦኤምኤን ተለይቶ እንደታየላቸው ያቀረቡትን መልስ አቃቤ ሕግ የሚቃወም መሆኑን ዛሬ ለፍርድ ቤት ባቀረበው መልስ አስታውቋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸው ክስ ቀሪ እንዲደረግና የዋስ መብታቸው እንዲከበር ያቀረቡትን ጥያቄ  ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከኦ ኤም ኤን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀዋር መሐመድ ጋር ተያያዥነት ያለው የሽብር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ከተጠረጠሩ ጀምሮ ያለዋስትና እስካሁን በእስር ላይ ይገኛሉ።

የዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰር ተከትሎ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የአውሮፓ ሕብረት የተቃውሞ መግለጫ በማውጣት በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በአስቸኳይ እንዲፈታቸው ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አላገኙም።