የፊላንዱ ቴንፐር ዩንቨርሲቲ ለጠቅላይ ሚንስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሊሰጥ ያሰበውን የክብር ዶክትሬት እንደማይሰጥ አስታወቀ

መጋቢት ፳ (ሃያ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዩንቨርሲቲው በድረገጹ ላይ ለጥፎት የነበረውን የጠቅላይ ሚንስትሩን ሽልማት ዜናም አንስቶታል። የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከአቶ ኃማሪያም ደሳለኝ ጋር የሚያገናኝ ምንም ዓይነት ቀጠሮ አለመያዙንም ገልጸዋል።
ዩንቨርሲቲው ለቀድሞው የቴንፐር ዩንቨርሲቲ ተማሪ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የክብር ዶክትሬት መስጠት ማሰቡን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ፣ በፊንላንድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት እንዲሁም በመላው አለም የሚገኙ ታዋቂ ሰዎች ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስልክ በመደወልና በትዊተር ዘመቻ በማካሄድ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ለእንደዚህ ዓይነት የክብር ሽልማት እሳቸውን ማጨት እራሱ አፍሪካዊያንን እንደ መናቅ እና መሳደብ ይቆጠራል። ለአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሽልማት መስጠት በንጹሃን ዜጎች ደም እንደ መቀለድ ነው ሲሉ ኢትዮጵያዊያኑ ተቌውመዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሞ እና አማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸማቸውን፣ ከአንድ ሽህ በላይ ንጹሃን ዜጎች በታጣቂዎች በግፍ መገደላቸውንና ከ30 ሽህ በላይ ዜጎች ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ቤት መታጎራቸውን እውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል ሲሉ ዩንቨርሲቲው ሃሳቡን እንዲቀይር ተጽእኖ አሳድረዋል።
ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው በበኩሉ ”በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በንቃት እከታተላለሁ። ጸረ ዲሞክራሲ የሆነውን አንባገነኑን ስርዓት በበላይነት የሚመሩትን ሰው ለሽልማት መምረጥ እንደ ስድብ ይቆጠራል። ይህ ውሳኔ እኔን በግሌ መስደብ ሳይሆን አፍሪካዊያንን በሙሉ በተለይ የኢትዮጵያን ሕዝብን እንደ መስደብ እቆጥረዋለሁ!” በማለት ለ የል ኒክተር ጋዜጣ ተናግሯል።
ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፊላንድ የኮሚኒቲ አባላት እንደገለጹት የሽልማቱ ስነስርዓት መሰረዙ አወንታዊ ነገር ቢሆንም፣ ኮሌጁ ኮሚኒቲው ለጻፈው ደብዳቤ ተገቢውን መልስ እስከሚሰጥ ድረስ ዘመቻቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ዩኒቨርስቲው አቶ ሃይለማርያም እንደማይገኙ በመግለጽ ሽልማቱን ማቆሙን ቢገልጽም፣ ይህ ግን ለሽልማቱ መሰረዝ የተሰጠ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል የኮሚኒቲው አባላት ይናገራሉ።