የፈረንሳይ የልማት ተራድኦ ቆሸን ለመለወጥ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ገንዘብ ሰጥቶ እንደነበር ተዘገበ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ብሎምበርግ ባወጣው ዘገባ የፈረንሳይ የልማት ተራድኦ እኤአ በ2011 በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቆሻሻ ናዳ ያለቁበትን ረጲ የቆሻሻ መድፊያ ወይም በተለምዶ ቆሸን ለመዝጋት ለአዲስ አበባ መስተዳደር 34 ሚሊዮን 600 ሺ ዩሮ መስጠቱን ገልጿል። ገንዘቡ የቆሻሻ መድፊያውን ለመዝጋትና ከአካባቢው ለሚነሱ ዜጎች መልሶ መቋቋሚያ ታስቦ የተለገሰ ነበር። በቆሸ የደረሰው አደጋ ፖለቲካዊ መሆኑን የዘገበው ጋዜጣው፣ የፈረንሳይ መንግስት ለሰንዳፋ የቆሻሻ መድፊያ ቦታም ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ እንደነበር ገልጿል።
የሰንዳፋ አርሶአደሮች ውሃቸው በቆሻሻ መበከሉን፣ እንስሶችም እየሞቱ መሆኑንና ሌሎችም ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን በመመልከታቸው በሰንዳፋ ቆሻሻ መደፋቱ እንዲቋረጥ ተቃውሞ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ተዘግቶ የነበረው ቆሼ እንደገና ስራ እንዲጀምር መደረጉ፣ ወትሮም በቋፍ ላይ የነበረው ቆሻሻ እንዲናድ አንድ ምክንያት መሆኑን የመስተዳድሩ ሰራተኞች ለጋዜጣው ተናግረዋል።