የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ

ሰኔ 14 ፥ 2009

መንግስት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የገንዘብ እጥረት እንደገጠመውና በጀት እንዳልመደበ ተገለጠ። የከተማ ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ ለፓርላማው እንዳስታወቁት፣ መንግስት በገጠመው የገንዘብ ችግር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን መቀጠል አልቻለም።

የ1997 ዓም ሀገራዊ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላለፉት 13 ያህል ዓመታት ቢቀጥልም መንግስት በ2ኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 750 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ቢያቅድም በገጠመው የፋይናንስ ዕጥረት ሂደቱ መገታቱ ተመልክቷል።

በ1996 ዓም ተግባራዊ የሆነው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እስካሁን በተገባው ቃል መሰረት ባይሄድም ከመቶ ሺህ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ መረዳት ተችሏል። ሆኖም  ከዓመት በፊት በታወጀው የ2ኛው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ቃል የተገባው 750 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤት በወጉ ሣይጀመር መገታቱን መንግስት አረጋግጧል።

ከ2005 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው 10/90፣ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ክፍያ ላጠናቀቁ ሰዎች መቅረብ እንዳልቻለም አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። በተለይም በ40/60 አንድም መኖሪያ ቤት ተገንብቶ አለመተላለፉን ለማወቅ ተችሏል።

በ1996 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤት ኮንደሚንየም ግንባታ የመኖሪያ ቤት ችግርን በማቃለል ተጠቃሽ ቢሆንም በጥራት ረገድ አያሌ ችግሮች ሲነሡበት ቆይተዋል፣ የሥነ ህንፃ ባለሙያዎች የቤቶቹ አሰራርና ቀለም በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ የከተማዋን ውበት በዘላቂነት ይጎዳል በማለት ሙያዊ ትችቶች ሲሠጡ ቆይቷል።