የገጠሩ ህዝብ የኢህአዴግን ጥሪ መቀበል አቁሟል ሲሉ የወረዳ አመራሮች ተናገሩ

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ በከተማው ህዝብ ሳይሆን በአርሶ አደሩ ድጋፍ እንደሚተማመን በተደጋጋሚ ይገ ልጸል። ምንም እንኳ አሁንም ከ6 ሚሊዮን ያላነሰ አርሶአደር በረሃብ መጠቃቱ እንዲሁም ከ7 ሚሊዮን ያላነሰ አርሶአደር በምግብ ለስራ መርሃ ግብር ታቅፎ በውጭ እርዳታ እየኖረ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ የግብርና ምርቱ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል። አርሶአደሩም መሰረታዊ የሚባሉት የምግብ፣ የጤና፣ የትምህርት ፍላጎቱ እየተሟሉለት መሆኑን ግንባሩ በየጊዜው ይለፍፋል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት በአደባባይ ይፋ ባያደርጉትም በራሳቸው መድረክ ላይ ግን በአደባባይ የሚናገሩትና በተግባር የሚታየው አንድ አለመሆኑን ይገልጻሉ።
የብአዴን የወረዳ አመራሮች በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች ስላለው የግብርና እንቅስቃሴና የአርሶደሩ ሁኔታ ሪፖርት እንዲያቀረቡ በተጠየቁበት ወቅት፣ ያቀረቡት ሪፖርት በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳይ ነው።
እቅዶች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝቡ ለታይታ ተብለው የሚዘጋጁ በመሆኑ ችግር እየፈጠረብን ነው የሚሉት አመራሮች፣ ሁሉም ሪፖርቱን ለውጤት ሲል እያጋነነ ፣ ያልተሰራውን እንደተሰራ አድርጎ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።
አርሶአደሩ ለተፈጥሮ ሃብት ልማት እንዲወጣ ሲታዘዝ እየተማረረ ነው የሚሉት አመራሮች፣ በግዳጅ እንዲወጣ ስለሚታዘዝ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም ይላሉ ፡፡
አርሶአደሩ ችግሮች መኖሩን እያየ እንኳን ብናገርም ምንም አላመጣም በሚል ሙስናን እንኳ ሳይቀር እንደማያጋልጥ የሚጠቅሱት አመራሮች፣ አርሶአደሩ ከወረዳዎች በሚሄዱ ባለስልጣናት ግራ እየተጋባ ነው ይላሉ።
የጤና እንቅስቃሴዎቻችን እጅጉን አሳፋሪ ናቸው የሚሉት አመራሮች፣ አርሶ አደሩ የህክምና አገልግሎት እያገኘ ነው ብለን ደፍረን ለመናገር የማንችለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል። መብራት ሳይገባ ከነበረን እይታ ይልቅ ከገባ ወዲህ እየተበሳጨን ነው የሚሉት አመራሮች፣ ጥቅም ሳይሆነ ኪሳራ ነው እያጋጠመን ያለው ይላሉ።
የወረዳ አመራሮቹ እንደሚናገሩት ህዝቡ በአጠቃላይ በድርጀቱ አመራሮች ላይ እምነት የለውም።