የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የቲማቲም ኩባንያ በአገሪቱ የሚታየውን የቲማቲም እጥረት ተከትሎ ከፍተኛ ሽያጭ እያካሄደ ነው

መጋቢት ፲፩ (አሥራ አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አሁን ለአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚወዳደሩት የህወሃቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ እና በአርሲ ዞኖች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ገዝተው የቲማቲም እርሻ እያኬዱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች የታየውን የቲማቲም እጥረት ተከትሎ፣ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ነው።
በአዲስ አበባ የቲማቲም ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን፣ 1 ኪሎ ቲማቲም እስከ 45 ብር ይሸጫል።
ይህ “East Africa” የሚል ስያሜ ያለው የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እርሻ 120 ቀርጥ ወይም ስፋቱ 30 ሄክታር ሲሆን፣ እርሻው ሙሉ በሙሉ የሚያመርተው ቲማቲም ነው። የቲማቲሙ እርሻ በዘመናዊ መንገድ የአጠና መደብ የተሠራለት ነው። ከእያንዳንዱ ቀርጥ እስከ 4 ቢያጆ ቲማቲም እየተጫነ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
የእርሻ ቦታው በቀድሞ ግዜ በመንግሥት የልማት ድርጅት ስር ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ አገዛዙ ለግል ባለሀብቶች ሲሸጠው የዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ዘመድ የሆነው አቶ ገብረ መስቀል አርአያ ገዝቶት ነበር። ይሁን እንጅ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከ2008 ዓ/ም ግማሽ አመት ጀምሮ ተረክበው እየሰሩበት ሲሆን፣ ቀድሞ የነበሩ የድርጅቱን ሠራተኞች ከግማሽ በላይ ተባረው የራቸውን ሰዎች ቀጥረዋል። ከእስራኤል ሀገር የመጡ የእርሻ ባለሙያዎችንም ተቀጥረው በመስራት ላይ ናቸው።
ከዚህ በፊት ያልነበረ የቲማቲም በሽታ ገብቶ የአካባቢው ገበሬዎች የሚያመርቱትን ቲማቲም ያወደመው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ለተፈጠረው የቲማቲም እጥረትም ይህ አንዱ ምክንያትም ነው። በበሽታው ያልተጎዳው የዶ/ር ቴዎድሮስ የቲማቲም እርሻ ብቻ መሆኑ፣ የአካባቢውን ህዝብ እያነጋገረ ነው።
ምንጮች እንደሚሉት በአገሪቱ የቲማቲም በሽታ መድሀኒት ብቸኛ አስመጪ እራሳቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ናቸው። እጅግ ውድ ከሆነው የመድሃኒት ሽያጭ ከፍተኛ ትርፍ እየሰበሰቡ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
አገሪቱ የቲማቲም እጥረት አጋጥሟት ባለበት ሰአት East Africa ቲማቲም ወደ ጂቡቱ ለመላክ ዝግጅት እያደረገ ነው።