የድርቅ አደጋ መከሰቱን ተከትሎ 175 ት/ቤቶች መዘጋታቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ 175 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች በዚሁ የድርቅ አደጋ ክፉኛ መጎዳታቸውን በድጋሚ ያወሳው ድርጅቱ በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት ተማሪዎች በመበራከታቸው ትምህርት ቤቶቹ ሊዘጉ መቻላቸውን ገልጿል። ከአደጋው ጋር በተገናኘ ከተዘጉት ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ 843 ሺ ሰዎች በአራቱ ክልሎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 456 ሺ 801 ፥ በኦሮሚያ 279 ሺ 867 ፥ በአፋር 51 ሺ 644 እንዲሁም በጋምቤላ ከግጭት ጋር በተያያዘ 18ሺ 503 ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ታውቋል። 

በጋምቤላ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች በግጭት ምክንያት መሆኑ ቢገለፅም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ ግጭቱ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም። ከወራት በፊት ከጎረቤት ሱዳን ዘልቀው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በትንሹ 28 ነዋሪዎችን ገድለው ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸው የሚታወስ ነው።

በዚሁ ጥቃት መንግስት በርካታ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ቢያረጋግጡም የነዋሪዎቹ ቁጥር እንዲሁም በታጣቂው ሃይሉ የተገደሉ የአካባቢው ነዋሪዎችን መጠን ሳይገልፅ ቆይቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ በክልሉ ተከስቶ ነበር ባለው ግጭት 18 ሺ 503 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ቢያመለክትም ጊዜውንና መንስዔውን ግን ከመግለፅ ተቆጥቧል። ድርጅቱ በተያዘው ሳምንት በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው ለሚገኙ 7.7 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆነው የምግብ አቅርቦት ከቀጣዩ ወር ሰኔ ጀምሮ ሊቋረጥ እንደሚችል ማሳሰቡ ይታወሳል።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለድርቁ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው የገንዘብ ልገሳ በወቅቱ ባለመገኘቱ ሳቢያ ድርቁ እየተባባሰ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

ይኸው የድርቅ አደጋ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ለአጣዳፊ ተቅማት ትውከት በሽታ ምክንያት መሆኑን ያወሳው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በስድስት ክልሎች 33ሺ 613 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን በሪፖርቱ አስፍሯል።

91 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ስርጭት በሶማሌ ክልል የተከሰተ ሲሆን፣ 780 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።