የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከሚያስፈልገው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መካከል 23 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከሚያስፈልገው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መካከል 23 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ተገለጸ።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠቱን ተከትሎ ድርቁ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የከፋ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት እና አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት በሃገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ከመንግስትና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሻለ ድጋፍ ተገኝቶ እንደነበር ያወሳው ወርልድ ቢዥን በዘንድሮው አመት የተከሰተው የድርቅ አደጋ ለመከላከ ግን ከሁለቱም ወገኖች የበጀት ጉድለቱ ከፍተኛ ሆኖ መቀጠሉን የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋሙን ዋቢ በማድረግ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ሚድያ አውታር (ኢሪን) ዘግቧል።

የወርልድ ቪዥን የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ኤድዋርድ ብራውን አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ለአለም አቀፍ እርዳታ የሚሰጡትን ድጋፍ በመቀነስ ላይ በመሆናቸው ድርቁን በመከላከል ዘመቻውን ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስረድተዋል።

በሃገሪቱ ዳግም ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መንግስት ለመከላከል እያካሄደ ባለው ዘመቻ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በ222 ጊዜያዊ መጠለያዎች 400ሺ አካባቢ የሚጠጉ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ተረጂዎች ቢኖሩም በ58 ጣቢያዎች ብቻ ያሉት ከመንግስት ድጋፍ እያገኙ መሆኑን የዜና አውታሩ በዘገባው አቅርቧል።

ከ222ቱ መጠለያዎች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑ የምግብ ድጋፍ እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ድርቁ በእስካሁኑ ቆይታው 200 ሚሊዮን ዶላር (ከአራት ቢሊዮን ብር) በላይ የሚገመት የእንስሳት ሞት ማስከተሉም ኢሪን አመልክቷል። በአራት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይነገራል።

የምግብ እጥረቱ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።

በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ 40 በመቶ አካባቢ የሚሆን የአካባቢውን እንስሳት እንደጨረሰ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በተለይ በሶማሌ ክልል የእንስሳት ሃብታቸውን ያጡ አርብቶ አደሮች ከድርቁ ሙሉ ለሙሉ ለማገገም እስከ 10 አመት እንደሚፈጅባቸውም ተመልክቷል።

በተያዘው አመት የበልግ ወቅት በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ መጣል የነበረበትን ዝናብ በተጠበቀው መጠን ባለመጣሉ ምክንያት ድርቁ እስከቀጣዩ አመት ድረስ ቀጣይ እንደሚሆን ተሰግቷል።

መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተርጂዎችን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን በቅርቡ ቢያረጋግጥም ቁጥሩን ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 5.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ከወራት በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይሁንና በእስከ አሁኑ ቆይታ 23.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ይፋ ተደርጓል።

በተያያዘ ዜና፣ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ መንግስት የድርቅ አደጋውን በራሱ እየተቋቋመ ነው ሲሉ ሃሙስ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ይሁንና የውጭ የእርዳታ ድርጅቶች እና ሃገራት የሚያደርጉት ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ ሃላፊው ጥሪን አቅርበዋል።

ድርቁን ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቢደረግም 93 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቷል ሲሉ አቶ ምትኩ አክለው ገልጸዋል።

መንግስት ድርቁን ለመታደግ ተገኝቷል ያለው ገንዘብ የእርዳታ ድርጅቶች ካስታወቁት ጋር የ69 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ልዩነት እንዳለው ታውቋል።

የውጭ ሃገር የእርዳታ ተቋማት ለተለያዩ የሰብዓዊ ዕርዳታ የያዙትን በጀት በሶማሌ ክልል ተከስቶ ላለው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ እንዲያዞሩት መጠየቃቸው አይዘነጋም።