የዳላስ ግድያ በኢትዮጵያኖች ላይ ሀዘንና ድንጋጤ ፈጥሯል

(Aug. 16) በዳላስ፤ ቴክሳስ የደስታ ሬስቶራንት ባለቤት በነበሩት አቶ ያየህ ይራድ ለማና ወ/ሮ የኔነሽ ደስታ ላይ በትላንትው እለት የተፈጸመው የግድያ ወንጀል በዳላስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ላይ ክፍተኛ ሀዘንና ድንጋጤ ፈጥሯል::
በዳላስ መልካም ስም ካላቸው የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የደስታ ሬስቶራንት ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ስራቸውን እኩለ ሌሊት ላይ አጠናቀው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲመለሱ መግቢያ በር ላይ የተገደሉት በጥይት ተመተው መሆኑ ታውቋል::
የ40 አመቱ አቶ ያየህ ይራድ በሁለት ጥይት፤ ወ/ሮ የኔነሽ ደግም በአንድ ጥይት ማንነቱ ባልታወቀ ነፍሰ ገዳይ ወይም ነፍሰ-ዳዮች ተመተው ህይወታቸው ወዲያው ማለፉ ታውቋል::
የዳላስ ፖሊስ ወንጀሉን በመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የተያዘ ተጠርጣሪ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል::
ሁለቱ ባልና ሚስቶች ትዳር ከመሰረቱ ጥቂት አመታት ያስቆጠሩ ሲሆን የ18 ወር ህጻን ልጅ ወላጆች ነበሩ::