የደደቢት ተጨዋቾች በክፍያ ምክንያት ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። የባህር ዳር ስፓርት ደጋፊዎች ተቃውሞ አሰሙ።

ሰኔ ፲፬( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ዋነኛ ተፎካካሪ እየሆነ የመጣውና ለየሊጉን ዋንጫ እስከማንሳት የደረሰው የትግራዩ ደደቢት እግር ኳስ ክለብበዘንድሮ አመት የውድድር ዘመን ለተጨዋቾቹ ደሞዝ ባለመክፈሉ በክለቡ ውስጥ ውዝግብ ተፈጥሯል።
ክለቡ የአምስት ወር ደሞዝ አልከፈለንም በማለት የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች የሆኑት አይናለም ኃይሌ ፣ አስራት መገርሳ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አክሊሉ አየነው እና ዳዊትፍቃዱ ልምምድ ካቋረጡ 15 ቀናትን አስቆጥረዋል፡፡
በርካታ ተጫዋቾች ደመወዛቸውን ባላገኙበት ሁኔታ ለተወሰኑ ተጫዋቾች በተለዬ መልኩ ለብቻቸው ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ውዝግቡን ይበልጥ አባብሶታል።
ደመወዛቸውን በመነፈጋቸው ልምምድ ያቋረጡት ተጫዋቾች በተደጋጋሚ በስልክም ሆነ በአካል ቢሮ ድረስ በመሄድ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው በቀጥታ ለክለቡ ያቀረቡትን ቅሬታቸውን በግልባጭ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብተዋል። ይሁንና ተጫዋቾቹ ላስገቡት የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ከክለቡ የተሰጣቸው ምላሽ ደብዳቤ የክለቡን ተጨዋቾች በማሳደም ለፈፀሙት ተግባር አስፈላጊውን እርምጃእንደሚወስድባቸው የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡
እንደ ሶከር ስፖርት ዘገባ ከአምስቱ ተጫዋቾች መካከል ዘንድሮ ቡድኑን ከተቀላቀለው አስራት መገርሳ በስተቀር አራቱተጨዋቾች በዘንድሮ አመት ከደደቢት ጋር ያላቸውኮንትራት የሚፈፀም ይሆናል።
በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት የተጫዋቾችን ክፍያ በከፍተኛ ደረጃ ያናረውና ስመጥር ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ከፍ ባለ ገንዘብ ሲወስድ የቆዬው ደደቢት አስራ አንድየሚሆኑ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ቢታወቅም፤ በዘንድሮ የውድድር አመት ክፉኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው በተለያየ ወቅት የክለቡ አመራሮችሲገልጹ ቆይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትርናንትናው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ሊካሄዱ የነበሩ ሁለት የእግር ኳስ ውድድሮች የመቀሌ ከነማና የሽሬ እንደ ሥላሴ ተጫዋቾች ለደህንነታችን ዋስትና ካልተሰጠን አንጫዎትም ማለታቸውን ተከትሎ ተሰርዘዋል።
ትናንት በባህድር ዳር እንዲካሄዱ ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበሩት ጨዋታዎች በአማራ ውሃ ሥራዎችና በመቀሌ ከነማ፣በሽሬ እንደስላሴ- እና በባህርዳር ከነማ መካከል የሚካሄዱ ነበሩ።
የትግራይ ክልል ክለብ ተጫዋቾቹ ለደህንነታቸው ዋስትና እስካልተሰጣቸው ድረስ እንደማይጫዎቱ ቢገልጹም ለዚህ ኃላፊነት የሚወስድ ባለመገኘቱ ነው ጨዋታው የቀረው።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአማራ ክልል ወጣቶች በላከው ደብዳቤ ጨዋታዎቹ ከባህር ዳር ውጪ በአዲስ አበባ እንዲካሄዱ ከክልሉ መንግስትና አንዳንድ ቢሮዎች የቃል ጥያቄ እንደቀረበለት ሆኖም ጥያቄውን በጽሁፍ እንዳልቀረበለት በመጥቀስ፣ ፌዴሬሽኑ በራሱ ጊዜ የውድድሩን ቦታና ቀን አውጥቶ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
ቡድናቸውን ለመደገፍ መቀሌ ስታዲየም በተገኙ የባህር ዳር ደጋፊዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ ይታወቃል። ይሁንና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጥፈተኛ በማለት ከባድ ቅጣት የጣለው በባህር ዳር ከነማ ላይ ነው።
በባለፈውም ሆነ ትናንት በተፈጠረው ሁኔታ የተበሳጩ የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች “የውሸት ፌዴሬሽን!” በማለት በፌዴሬሽኑ ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።