የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የነጻነት በአል አይከበርም አሉ

 

(ኢሳት ዜና – ሀምሌ 3/2009) ደቡብ ሱዳን ስድስተኛውን የነጻነት ቀንን በፌሽታና በፈንጠዝያ እንደማታከብር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር አስታወቁ።

 

ሳልቫኪር እንዳሉት ሀገሪቱ ከገጠማት ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ በአሉን በአደባባይ ከፍተኛ ወጭ አውጥታ ላለማክበር ወስናልች።

 

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት በሀገሪቱ እየተባባሰ ለመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ተደርጎ ተቀምጧል።

 

ከዚህ ጋር በተተያያዘም ይላሉ ሳልቫኪር የሀገሪቱ ዜጎችን ከችግር ለማውጣት አላግባብ የሚባክን ገንዘብ መኖር የለበትም።

 

ሳልቫኪር አክለውም በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣው ሙስናና የነዳጅ ገቢ ማሽቆልቆል ለችግሩ ምክንያት ነው ብለዋል።  ይህ ደግሞ 98 በመቶውን የሀገሪቱን ገቢ ጎድቶታል።

 

በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅም በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዳያረጋግጡ አድርጓል ብለዋል።

 

አለማቀፉ ማህበረሰብ በሀገሪቱ የተከሰተውን ይህን ችግር ለመቅረፍ ብሄራዊ ውይይት እንዲደረግ እንዲያግዝ ሳልቫኪር ጥሪ ማቅረባቸውን በካርቱም የሚታተመው ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ ዘግቧል።