የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በጋምቤል ክልል ጥቃት ፈጽመው 28 ሰዎችን ሲገድሉ 43 ህጻናትን ጠልፈው መውሰዳቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2009)

ሰሞኑን ከደቡብ ሱዳን ድንበር በመዝለቅ በጋምቤላ ክልል ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎች 28 ሰዎች መግደላቸውንና 43 ህጻናትን ዳግም አግተው መውሰዳቸውን መንግስት አረጋገጠ።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በፈጸሙት ጥቃት ከ100 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውንና ወደ 125 አካባቢ የሚደርሱ ህጻናት ታፍነው መወሰዳቸው ይታወሳል። ይኸው ጥቃት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በድጋሚ መፈጸሙንና በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ኢሳትና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ምላሽን የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ታፍነው የተወሰዱት ሰዎችን ለማስለቀቅ መንግስት በድንበር አካባቢ የጸጥታ ሃይል ማሰማራቱን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ስፍራዎችን ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት 18 ሰዎች መገደላቸውንና ወደ 30 አካባቢ ህጻናትን ዳግም አግተው መውሰዳቸውን ሃላፊው አረጋግጠዋል።

ዶ/ር ነገሪ የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው መሰማራቱን ቢናገሩም የጸጥታ አባላቱ የደቡብ ሱዳን ግዛትን አቋርጠው ይግቡ አይግቡ የሰጡት መረጃ የለም።

ባለፈው አመት የሙርሌ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ተመሳሳይ ጥቃት ተከትሎ የመንግስት በርካታ ወታደሮችን ወደ ደቡብ ሱዳን ግዛት አስገብቶ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ምንም አይነት ዕርምጃ ሳይወስድ መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ከታጣቂ አባላቱ ጋር ድርድር በማካሄድ ከታገዱ ከ100 በላይ ህጻናት መካከል ወደ 80 የሚሆኑት በወራት ጊዜ ውስጥ መልቀቅ መቻላቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በወቅቱ አስታውቋል።

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ዕልባት ለመስጠት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስት ጥቃት የፈጸሙትን አካላት ለህግ ያቀርባል የሚሉት ሚኒስትሩ ትልቁ ጉዳይ አካባቢውን ማልማት ነው በማለት ምላሽን ሰጥተዋል። ይሁንና ባለፈው አመት ጥቃት ከፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አመቺ የሆኑ ጊዜያት በመምረጥ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ባለፈው አመት የጎሳ ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ20 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በእሳት መውደማቸው የሚታወስ ነው።

የደቡብ ሱዳን መንግስት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በተለያዩ ጊዜያት ጥረትን ቢያደርግም፣ ጥረቱ ሊሳካ አለመቻሉን ለመረዳት ተችሏል።

የጎሳ ታጣቂዎች ድርጊቱን በምን ምክንያትን እንደሚፈጽሙ የታወቀ ነገር የለም።