የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳል-ባኪር ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ሃሙስ አዲስ አበባ ገቡ

ኢሳት (የካቲት 16 ፥ 2009)

በግብፅ ጉብኝትን በማድረጋቸው ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳል-ባኪር ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ሃሙስ አዲስ አበባ መግባታቸው ተገለጸ።

ፕሬዚደንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በሚሻሻልበትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ መጠበቁን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።

ፕሬዚደንት ኪር በቅርቡ በግብፅ ባደረጉት ጉብኝት ከግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ጋር የአባይ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ የጸጥታ ጉዳዮች ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና ሁለቱ ሃገራት በመገንባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ እና በወንዙ የመብት አጠቃቀም ላይ ደርሰውታል የተባለው ይፋ ያልተደረገ ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል ቅሬታ አሳድሮ መቆየቱን በርካታ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

የደቡብ ሱዳን እና ግብፅ የአባይ ግድብ ግንባታ የሌላ ሃገርን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን አለበት የሚል ሃሳብን አንስተው መወያየታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አለመግባባት ውስጥ ገብቷል መባሉን ተከትሎም ፕሬዚደንቱ ሳልባኪር ሃሙስ አዲስ አበባ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ በግብፅ ተደርሰዋል የተባሉ ስምምነቶች በዚሁ ምክክር ወቅት ሊነሱ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

ፕሬዚደንት ሳል-ባኪር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱ ሃገራትን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ይፈራረማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አሜሪካ በደቡብ ሱዳን መንግስትና በአማጺያን በኩል ያለው አለመግባባት ዕልባት እንዲያገኝ ፍላጎት እንዳላት ባለፈው ሳምንት ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት እንዲደርሱ ቢያደርጉም ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ግጭት በማምራታቸው የጋራ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተደረሰው ውሳኔ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ይነገራል።

በደቡብ ሱዳን መንግስትና በአማጺ ቡድኑ መካከል በድጋሚ የተቀሰቀስውን ግጭት ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ መሪ  ወደ ደቡብ አፍሪካ የኮበለሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የአማጺ አመራሩ ሪክ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።

ፕሬዚደንት ሳልባኪር  በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ በዚሁ የአማጺ ቡድን የሰላም ስምምነት ዙሪያ አደራዳሪ ከነበሩት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ለመረዳት ተችሏል።