የየካ ክፍለ-ከተማ ነዋሪዎች ፤የኢህአዴግ ልማት ኮሚቴ የጠሩትን ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸው ተዘገበ

ህዳር 6 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የየካ ክፍለ-ከተማ ነዋሪዎች ፤የኢህአዴግ ልማት ኮሚቴ የጠሩትን ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸው ተዘገበ።  ህዝቡ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ እያመፀ ነው፡፡  በሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች  ስብሰባውን ረግጠውና የስብሰባውን አዳራሽ ጥለው ለመውጣት የተገደዱት ፤በአዲሱ የመሬት ሊዝ አዋጅና በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ እንዲሁም በሊዝ የክፍያ ስርዓትና ባለይዞታዎች በካሬ ሜትር እንዲከፍሉ በተተመነው ገንዘብ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው ከመድረክ ምላሽ ስለተነፈጋቸው  መሆኑ ታውቋል፡፡

ህዝቡ “ልማትን” አስመልክቶ ለመወያየት የተደረገለትን ጥሪ በማክበር ዕሁድ ሕዳር 3 ቀን 2004 ዓ.ም ከፈረንሳይ ኤምባሲ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ፈረንሳይ መናፈሻ የስብሰባ አዳራሽ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ  የተገኘ ቢሆንም፤ከውይይቱ መጀመር በፊት ነዋሪው የመሬትና የሊዝ፣እንደዚሁም የይዞታ ማረጋገጫ ጉዳይ በአጀንዳ እንዲያዙለት ጥያቄ ማቅረቡን ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል፡፡

የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የመድረኩ መሪዎች ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም ፤ለውይይት የታደመው ነዋሪ፦  “ከልማት በፊት የመሬት፣የሊዝና የመሬት ክፍያ አፈፃፀም ጉዳይ ይቅደም! . . .” በሚል ጠንካራ አቋም መጽናቱን የጠቀሰው ፍኖተ-ነፃነት፤ በዚህም ሳቢያ  ውዝግቡ ይበልጥ እየተካረረ ሄዶ ለስብሰባ ከተጠራው ሕዝብ መካከል አብዛኛው አዳራሹን በቁጣ ለቅቆ በመውጣት ቅያሜውን ገልጿል ብሏል፡፡

ነዋሪውን ሕዝብ ለመንገድ ልማት መዋጮ አስፈላጊነት እንዲወያይ ጠርተውት የነበሩት የየካ ክፍለ-ከተማ የልማት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ተጠሪዎችም በሁኔታው ተደናግጠው መታየታቸው ታውቋል።

የክፍለ-ከተማው ሀላፊዎች በአዳራሹ ከቀሩት ጥቂት ነዋሪዎች ጋር  ስብሰባውን በመቀጠል- ስለ ልማት መዋጮ አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲሞክሩም፦ “ሕዝቡ መዋጮ የመስጠት አቅም ላይ አይደለም . . .” የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡

በተለይ ከተሰብሳቢዎቹ አንድ ግለሰብ ከመቀመጫቸው በመነሳትና በሀይለ ቃል፦ “ሕዝቡ በአብዛኛው በጡረታና በድጎማ የሚኖር፣ባለፈው ሥርዓት በውትድርና ሙያ አገሩን ሲያገለግል የነበረና በአሁኑ ወቅት የተረሳ በመሆኑ የገዛ ኑሮውን እንኳን ለማቃናት ተቸግሯል፡፡ እንደዚሁም ሆኖ ከዚህ በፊት ለጤና፣ለትምህርት፣ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት፣ለዓባይ ግድብ ወዘተ እየተባለ የአቅሙን ያህል አዋጥቷል፡፡ ለመንገድ ልማት እየተባለም ያላዋጣበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ይሰራል የተባለው መንገድ አልተሠራም፡፡ እንደገና ዛሬም ለመንገድ መዋጮ ክፈል ይባላል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ለአካባቢ ልማት ያለውን ከመስጠት አልቦዘነም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ለመሬት ካርታ የተጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል አቅም የለውም ” በማለት ነዋሪው  ያለበትን ችግር  አንጸባርቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ህዝቡ አዲስ በወጣው የሊዝ አዋጅ ላይ ማመፅ መጀመሩ ተሰምቷል። በየካ ክፍለ-ከተማ ከሚገኙት  8 ሺህ ነዋሪዎች መካከል ፤“ንብረት አልባ አድርጎ በሚያስቀረው” በአዲሱ  አዋጂ መሰረት   የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እንዲወስዱ ለቀረበው ጥሪ ፤ ከ6 ሺህ የሚበልጠው ህዝብ አኩርፎና አምጾ   ጥሪውን ሳይቀበል መቅረቱ ታውቋል።

አዲሱ የሊዝ አዋጅ  ውዝግብ በፈጠረበት በዚሁ ህዳር 3 ቀን በተካሄደው ስብሰባ ላይ፤የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወጥቶላቸው እንዲወስዱ የስም ዝርዝራቸው በየቀበሌው ከተለጠፈ የየካ ክፍለ ከተማ 8ሺህ ነዋሪዎች መካከል 2ሺህ ሰዎች ብቻ ወደ የቀበሌው ጽ/ቤት በመቅረብ ስለተጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆን አቤቱታ ማሰማታቸው ፤  ከ 2 ሺዎቹ መሀከልም የተተመነላቸውን ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑት በጣም ጥቂት እንደሆኑና የተቀሩት ክፍያው በጣም እንደበዛባቸውና ሊቀነስላቸው እንደሚገባ ጥያቄ ማቅረባቸው ተመልክቷል።
ከነዚህ ውጪ የሆኑት 6 ሺህ የክፍለ- ከተማው ነዋሪዎች ግን ወደ የቀበሌው ዝር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን  ራሳቸው  የክፍለ-ከተማው ተወካይ በዕለቱ  ለተሰበሰቡት ነዋሪዎች በግልጽ መናገራቸው ተሰምቷል።