የዝዋይ ሃይቅ በኬሚካል በመበከሉ ህዝቡ ውሃውን እንዳይጠቀም ተከለከለ

የካቲት ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሆላንድ ዜጎች የተመሰረተውና ከፍተኛ መንግስታዊ ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት ሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ የሚጠቀምበት ኬሚካል የዝዋይ ሃይቅን በመበከሉ፣ ህዝቡ ውሃውን እንዳይጠቀም ተከልክሏል። ክልከላው በቀበሌ ደረጃ ከተላለፈ ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ ህዝቡ በከፍተኛ የውሃ ችግር እየተሰቃየ ነው።
ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለፁት ከዝዋይ ሃይቅ ተጣርቶ የሚወጣው የቧንቧ ውሃ ሲመረመር ከፍተኛ የሆነ ለጤና አደገኛ የሆነ ኬሚካል የተገኘበት ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ ውሃው እንዳይጠጣ ተከልክሏል። ምርመራው የተደረገው ውሃውን የሚጠቀሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ህመም እየተዳረጉ መምጣታቸውን ተከትሎ ነው። አቅም ያለው ሰው ከቡልቡላ ወንዝ የሚቀዳውን ውሃ በጀሪካን እስከ 20 ብር እየገዛ ሲሆን፣ አቅም የሌለው ሰው ግን ከመሞት በሚል አሁንም የሃይቁን ውሃ እየተጠቀመ ነው ።
ውሃው በሚፈስበት አካባቢ ግድብ መገደብ ቢጀምሩም፣ ፍሰቱን የሚከላከል እንዳልሆነና የሚገልጹት ነዋሪዎች የአበባ እርሻው ከአካባቢው እስካልተነሳ ድረስ በህዝብ ላይ ጉዳት ማድረሱን ይቀጥላል ብለዋል።
የውሃውን መበላሸት ተከትሎ እንስሳት መጎዳታቸውን እንዲሁም በሃይቁ የነበሩ አሳዎች እያለቁ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሼር የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።