የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከሶስት ወር ያነሰ የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ብቻ ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑ ተመለከተ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2009)

የብሄራዊ ባንክ የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከሶስት ወር ያነሰ የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ብቻ ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑን የባንኩ አረጋገጠ። በአስመጪ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ በርካታ ነጋዴዎች ሃገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት በአማካኝ እስከ ስድስት ወር ወረፋን እንደሚጠብቁ ሲገልፁ ቆይተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ለፓርላማ የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ረቡዕ ያቀረቡት የባንኩ ዋና ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የ2.3 ወራት የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የገቢና የወጪ ንግድ አለመመጣጠን ለውጭ ምንዛሪ ማሽቆልቆሉ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አቶ ተክለወልድ ለፓርላማ የፋይናንስ በጀት ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል። የሃገሪቱ የውጭ ንግድ ካለፉት ሶስትና አራት አመታት ወዲህ ቅናሽ ማስመዝገቡ እንዲሁም አጋጥሞት ያለው የፋይናንስ ችግር ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምክንያት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች ሃገሪቱ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ማግኘት የቻለችው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን፣ ለገቢ ንግድ ግን 11.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከውጭ ንግድ የተገኘው ገቢ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ቢሆንም ባለፉት ስድስት ወራት በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2.4 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘታቸውን የብሄራዊ ባንክ መረጃ የመለክታል።

የአለም ባንክና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ተግባራዊ እንድታደርግና ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ሃሳቡን መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት ምላሽን የሰጡ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ግን የአንድ ዶላር ምንዛሪ ከ26 ብር በላይ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በባንኮች በኩል አንድ የአሜሪካን ዶላር በ 22 ብር 86 ሳንቲም እየተገዛ ይገኛል።

የአፍሪካ ሃገራት አማካኝ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አራት ወር አካባቢ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻር እና የንግድ እንቅስቃሴ ጋር ሲነጻጸር ያላት ከሶስት ወር በታች የውጭ ምንዛሪ ክምችት አቅም ዝቅተኛ መሆኑታውቋል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ታህሳስ 2015 ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እና ወርቅ ክምችት 3.5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁንና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሃገሪቱ ያላትን አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከመግለጽ ተቆጥቧል።

በሃገሪቱ የተከሰተውን ይህንኑ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ አዲስ መመሪያን በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡም ሆነ ከሃገሪቱ የሚወጡ መንገደኞች በእጃቸው የያዙትን የውጭ ሃገር ገንዘብና ጌጣጌጥ እንዲያስመዘግቡ መደረጉ ይታወሳል።

ይሁንና የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጄክቶች በቂ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ላይ ክፍተት አልነበረም ሲሉ አክለው አስታውቀዋል።