የዋልድባ ገዳም ምእመናን በገዳሙ ዙሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል

መጋቢት 17 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የሚካሄደው የስኳር ልማት ለገዳሙ ህልውና አደጋ ደቅኗል ያሉ ምእመናን በገዳሙ ዙሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል።

የተቃውሞው መጠን ያሰጋው መንግስት ሰሞኑን በአካባቢው ያሉ ከ300 በላይ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ሰብስቦ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መክፈታቸውን ገልጦ፣ የዋልድባ ገዳምን ሰበብ አድርገው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩትን እንዲቆጣጠሩ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጅ አንድ በስብስባው ላይ የተሳተፈ የኢህአዴግ አባል እንደተናገረው በስብሰባው ወቅት ከሁለት የህወሀት አባላት በስተቀር ሁሉም የኢህአዴግ አባላት መንግስት በገዳሙ ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ጠይቀዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ/ም በገዳሙ ተገናኝተው የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። ከፍተኛ ህዝብ ይገኛል ተብሎ በታመነበት በዚሁ ቀን፣ ግጭት ሊነሳ ይችላል በሚል መንግስት የጸጥታ ሀይሉን ወደ ስፍራው ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው።

አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ ነዋሪ በ27 ቁርጥ ነው፣ መንግስት ገዳማትም ማውደሙን ካላቆመ  የመዳህኒአለም እሳት ይበላዋል፣ የአካባቢው ሰው ያችን ቀን በጉጉት እየጠበቀ ነው ብሎአል።

ምንም እንኳ መንግስት ፕሮጀክቱ ለገዳሙ ህልውና ስጋት አይሆንም በማለት ቢናገርም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሚቀበሉት አልሆነም።