የዋልድባ ገዳም መነኮሳት በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ተዘገበ

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው መነኮሳቱ በጎንደር ከተማ በነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ተብለው ይፈለጉ ለነበሩ ግለሰቦች ከለላ ሰጥተዋል በሚል ምክንያት የሽብርተኝነት ክስ ተከፍቶባቸዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ሰኔ 20/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ላቀው የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ 35 ግለሰቦችን ክስ በንባብ ያሰማ ሲሆን ከተከሳሾቹ መካከል ሁለቱ፤ አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም ካሴ እና አባ ገ/ስላሴ ወ/ሀይማኖት የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ናቸው፡፡
በክስ መዝገቡ ስር ያሉት ተከሳሾች 6 ክሶች የተመሰረተባቸው ሲሆን ከቀረቡት ክሶች መካከል ከ5ኛ ክስ ውጭ ያሉት ክሶች በ1996 የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32/1/(ሀ)(ለ) (38) እና በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ከእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ አስማረ ብሩ፣ ግርማቸው (ቅዱስ)፣ ከኢሳት ጋዜጠኞችና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመገናኘትና ገንዘብ በመቀበል በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ፣ በደንቢያ፣ በአርማጭሆ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና ቤንሻንጉል መተከል ዞን አካባቢዎች ለሚገኙ ታጣቂዎች መሳሪያ፣ ጥይትና ቁሳቁስ አቀብለዋል የሚል ይገኝበታል፡፡ ከዚህም በተጫማሪ ለታጣቂዎችና ውጭ ሀገር ይገኛሉ ለተባሉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች መረጃ ሲያቀብሉ ነበር በሚል በማሴር፣ በመደራጀትና ሽብር ለመፈፀም ሙከራ በማድረግ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
5ኛ ክስ በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7(1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ገንዘብ በማስላክ፣ መሳሪያ በመግዛት፣ ቁሳቁስና መረጃዎችን ለታጣቂዎቹ በማድረስና ለአመራሮቹና ለታጣቂዎች መረጃ በማድረስ በሽብር ወንጀል መሳታፋቸውን፣ በ6ኛ ክስ በ34ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ደግሞ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞን እንዲሁም ባህር ዳር አካባቢ ለሚገኙ ታጣቂዎች ስልጠና ሰጥቷል የሚል ነው፡፡ 21ኛ እና 22ኛ ተከሳሾች ቤንሻንጉል ክልል መተከል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብሎ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደርና ባህር ዳር ከተማ በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ተሳታፊ እንደነበሩ ክሱ ላይ ቀርቧል፡፡
ተከሳሾቹ ከአሁን ቀደም ሌላ ክስ ከቀረበባቸው ንግስት ይርጋ እና አታላይ ዛፌ እንዲሁም አርማጭሆና ወልቃይት አካበቢ የነበሩ ታጣቂዎችን ይመራ ነበር ከተባለው ጎቤ መልኬ ጋርም ግንኙነት ነበራቸው የሚል የክስ ዝርዝር ቀርቦባቸዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በባህርዳር ዙሪያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ምንም አይነት የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ እንደሌለ የኢሳትን ዘገባ በማጣጣል በተለያዩ ዘዴዎች ሲያስተባብል ቢቆይም፣ የአቃቢ ህግ ክስ በእነዚህ አካባቢዎች ትግል ሲካሄድ እንደነበርና አሁንም እየተካሄደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት ተሳትፈዋል የተባሉ የመኢአድ አባላት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ጋዜጠኛ ጌታቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው፣ በአማራ ክልልና አዲስ አበባ ውስጥ በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱ የግንቦት ሰባት አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር አመፅ አነሳስተዋል በተባሉት አቶ ዘመነ ጌቴ ቦጋለ እና አቶ ለገሰ ወልደሃና ጥላሁን ላይ የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አቶ ዘመነ ጌቴ ከአቶ ዘመነ ምህረትና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመገናኘት፣ ሰሜን ጎንደር ለሚንቀሳቀሱ የግንቦት 7 ታጣቂዎች ቁሳቁስ አቅርቧል፣ ትዕዛዝ ሰጥቷል እንዲሁም ተቀብሏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
አቶ ለገሰ ወልደሃና በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገፆች ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሱ ፅሁፎች እንደለቀቀ በክሱ የቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የፍርድ ቤት ውሎ፣ የግፍ ፍርድ ተፈረደ፣ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ፣ በጨለማ የሚኖረው አርሶ አደር ለምን ለግድቡ እንዲከፍል ይገደዳል? የጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነት፣ የጨለማ ዘመን ከኢትዮጵያ ማህደር…. እና ሌሎችም በድረገፆች ቀረቡ የተባሉ ፅሁፎች በክሱ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡
ከሁለቱ የመኢአድ አባላት በተጨማሪ ሌሎች 8 ተከሳሾችም በዚሁ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32/1/(ሀ)(ለ) (38) እና በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3(1) እና 4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ለታጣቂዎች ገንዘብ በማዋጣት፣ የጦር መሳርያ በመግዛትና ፈንጅ በማፈንዳት የሰው ህይወት እንዲያልፍ አድርገዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።