የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሐገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 26/2009) የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሐገሪቱ በቅርቡ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ውሳኔ ሰጠ።

በኬንያ በተቃዋሚው እጩ ፕሬዝዳንት ራይላ ኦዲንጋ የሚመራው ፓርቲ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ክስ መስርቶ ነበር።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በተቃዋሚዎች የቀረበውን ማስረጃና ክርክር አድምጦ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኬንያውያን ድምጽ ሰጥተው የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አሸንፈውበታል የተባለውን ምርጫ ሰርዞታል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫው እንደገና ይካሄድ የሚለው ፍርድ ባይዋጥልኝም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ግን አከብራለሁ ብለዋል።

የኬንያው ጠቅላይ ፍርድ ቤት 7 አባላት ያሉትና የመጨረሻው ውሳኔ ሰጭ የፍትህ ተቋም ነው።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሀሴ 8/2017 ከመካሄዱ በፊት ተቃዋሚዎችም ሆነ መላው ኬንያውያን በሐገሪቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ እምነት እንዳላቸው ሲገልጹ ነበር።

ይህንኑ በተመለከተም ከምርጫው በፊት አስተያየታቸውን የሰጡን በአሜሪካ ጆርጅ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ዮሐንስ ገዳሙ ስለምርጫውና ስለኬንያ የዲሞከራሲ ተቋማት ጥንካሬ ሒደት ለኢሳት እንዲህ ብለው ነበር።

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዮሐንስ ገዳሙ በወቀቱ እንዳሉት የኬንያ የፍትህ ተቋማት ለአፍሪካ ትምሀርት የሚሰጡ ናቸው።በኢትዮጵያ ባለው የምርጫ ሂደት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ፍርድ ቤቶች ሳይቀሩ የገዥው ሕወሀት/ኢሃአዴግ ፓርቲ መጫወቻ ናቸው ማለታቸውም ይታወሳል

የኬንያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአብላጫ ድምጽ አሸንፈዋል ቢባልም ተቃዋሚያቸው ራይላ ኦዲንጋ ሒደቱ ተፋልሷል ፥ ማጭበርበርም ተፈጽሟል በሚል ውጤቱን አልተቀበሉትም ነበር።
ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ይፋ ከተደረገና የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደጋፊዎች ደስታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ግን እተማመንበታለሁ ወዳሉት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማምራት የተቃውሞ አቤቱታቸውን በጠበቆቻቸው አማካኝነት አቅርበዋል።

ሰባት አባላት ካሉት የኬንያ ፍርድ ቤት 6ቱ በተገኙበት የፍርድ ክርክርና እሰጣገባ በኋላ ታዲያ የምርጫውን መሰርዝ እና እንደገና እንዲካሄድ የሚለውን የመጨረሻ ውሳኔ ዋናው ዳኛ ዴቪድ መርጋ ይፋ አድርገዋል።

ዋናው ዳኛ ዴቪድ መርጋ እንዳሉት በህገመንግስቱ በተቀመጠው የህግ የበላይነት መሰረት ጉዳዩን በመመርመር ምርጫው ተሰርዞ እንደገና እንዲካሄድ 4 ለ 2 በሆነ አብላጫ ድምጽ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተወስኗል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ የተቀበሉት ራይላ ኦዲንጋ በአፍሪካ የዲሞክራሲ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ሲሉ ወሳኔውን እና ዳኞቹን አወድሰዋል።
እናም ድሉ ለኬንያውያን ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን ነው የገለጹት።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው የተሰጠው ፍርድ ባይዋጥላቸውም ለሕግ በመገዛት የጠቅላይ ፍርድቤቱን ውሳኔ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በቀጣዮቹ 60 ቀናት ውስጥ እንደገና መካሄድ ይኖርበታል።