የኬኒያ ፖሊስ 40 ህገወጥ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መያዙን አስታወቀ

ሰኔ ፩ ( አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ረቡእ ምሽት ላይ በማና ክፍለሃገር ኬዮሌ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በአንድ ትንሽ ቤት ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ ተቀምጠው እያሉ መያዛቸውንና እድሜያቸው ከ10 እስከ 25 ዓመት የሚሞላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች መሆናቸውንም ፖሊስ አስታውቋል። ከመሃከላቸው የእንግሊዝኛም ሆነ የስዋሂሊ ቋንቋ ተናጋሪ የለም። እንዴት ወደ ኬንያ እንደገቡ ፖሊስ በማጣራት ላይ መሆኑንም የአገሪቱ የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣናት ገልጸዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ኪዮሌ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አስተርጓሚ ሲገኝ ጉዳያቸው እንደሚታይላቸው ናይሮቢ ኒውስ ዘግቧል።
ገዥው ህወሃት ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ባለሁለት አሃዝ ምጣኔሃብታዊ ለውጥ አምጥቻለው እያለ በየእለቱ በመገናኛ ብዙሃን ቢገልጽም፣ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ግን ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በአራቱም መአዘናት መፍለሳቸውን ቀጥለዋል። በቅርቡ በጦርነት ወደምትታመሰው የመን ባሕር አቆራርጠው ከሚገቡ ስደተኛኦች ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም /IOM/ መግለጹ ይታወሳል።